(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 11/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከጎንደር ህዝብ ጋር በሚያደርጉት ውይይት ላይ የተደራጁ ግለሰቦችን በማስገባት የወልቃይትን ጉዳይ የጸረ ሰላም ሃይሎች አጀንዳ ተደርጎ እንዲቀርብ ሕወሃት በዝግጅት ላይ መሆኑ ታወቀ።
ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ እንደተመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ከህዝብ የሚያጋጭ ሌላ ፍጥጫ በጎንደር ለመፍጠር የተዘጋጁ ግለሰቦች ስልጠና መውሰዳቸውም ታውቋል።
በቅማንት የመብት ጥያቄ ስም የተደራጁት እነዚህ ግለሰቦች የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብአዴን የቅማንትን ጥያቄ ለማድበስበስ በሚል የወልቃይትን ጉዳይ እያጠነጠነው ነው የሚል ክስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያቀርቡ ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነገ ጎንደር ይገባሉ። በፋሲል ስታዲየም በሚደረገው የአቀባባል ፕሮግራም ላይ ለጎንደር ህዝብ ንግግር ያደርጋሉ። በማግስቱ ቅዳሜ ሚያዚያ 13 ለተመረጡ የከተማዋ ነዋሪዎች፡ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በተዘጋጀው የውይይት ፕሮግራም ላይ ይሳተፋሉ።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚደረገው ውይይት የሚሳተፉት ሰዎች በድርጅት መስመር የተመረጡ፡ በፖለቲካዊ ታማኝነታቸው የተመዘኑ፡ በተለይም ከህወሀት አንጻር የተሳሳተ አቋም የላቸውም ተብለው የሚታመኑ እንደሚሆኑ ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ ተመልክቷል።
በመቀሌው ስብሰባ የወልቃይትን ጉዳይ የልማት ጥያቄ ነው በማለታቸው ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበባቸው የሚገኙትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ከአማራ ህዝብ ጋር ለማጋጨት የህወሀት አገዛዝ አጋጣሚውን ሊጠቀም መዘጋጀቱን የሚያሳይ መረጃ ለኢሳት ደርሲታል።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ነገ ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ/ም በጎንደር ከተማ በፋሲል ስታዲየም የሚያደርጉት ንግግርም ተቋውሞ ሊገጥመው እንደሚችልም እየተነገረ ነው ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከተመረጡ የጎንደር ነዋሪዎች ጋር በሚያደርጉት ውይይት የወልቃይትን ጥያቄ የሚያጥላሉ፡ በምትኩም የቅማንተን ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው የሚጠይቁ ሰዎች በህወሀት በኩል ተዘጋጅተው ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
የቅማንት ማህበረሰብን እንወክላለን የሚሉ የኮሚቴ አባላትና ሌሎች በጥቅም የተስማሙ ግለሰቦች በሮቤት እና በትክል ድንጋይ ከተሞች ስልጠና እንደወሰዱ ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በዋነኛነት የወልቃይት ጥያቄ የሚባል የለም፡ ይህን ጥያቄ ብአዴን ያቀነባበረው ነው በሚል የተመረጡ ንግግሮችን እንዲያደርጉ የተመለመሉ ናቸው።
የቅማንትን የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄን ለማዳፈን በሚል በብ አዴን የተፈጠረ ጥያቄ እንጂ የወልቃይት ማንነት ተረጋግጧል ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቀሌ የያዙትን አቋም እንዳይቀይሩ ጫና ለመፍጠር መታቀዱንም ለማወቅ ተችሏል።
የብአዴን አመራሮች በቅማንት ሕዝብ በደል እና ግድያ በመፈጸማቸው ለፍርድ ይቅረቡልን የሚል ጥያቄም እንዲያቀርቡ በስልጠናው ወቅት መመሪያ እንደተሰጣቸው ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ህወሀት ባዘጋጀው ወጥመድ ውስጥ ገብተው የመቀሌውን ስህተት የሚደግሙ ከሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ የሚነሳ እንደሚሆን ህዝቡ እየተነጋገረበት ነው ሲል የኢሳት ወኪል ከስፍራው ገልጿል።
አሁን ዘግይቶ በደረሰን ዜና በጎንደር ከተማ በተሽከርካሪ ባለንብረቶችና በመንግስት ባለስልጣናት መሀል ግጭት መፈጠሩ ተገለጸ።
ዛሬ ከቀትር በኋላ በጎንደር ከንቲባ አዳራሽ የተጠሩት የየአገር አቋራጭ አውቶብስና የሌሎች የህዝብ ማመላለሺያ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች በነገው ዕለት ወደ ጎንደር የሚመጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለመቀበል ከተለያዩ የጎንደር ዙሪያ አከባቢዎች የሚገቡ ሰዎችን በነጻ እንዲያመላልሱ በመጠየቃቸው በተነሳ ተቃውሞ ነው።
ባለንብረቶቹ ክፍያ ሲጠይቁ፡ ባለስልጣናቱ ግን ይህ ሀገራዊ ጉዳይ በመሆኑ አገልግሎቱን በነጻ እንዲያደርጉ በማስፈራራት ጭምር መጠየቃቸው ተከትሎ ግጭት ተፈጥሯል።
የኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ በመሆኑ ማክበር አለባችሁ አለበለዚያ የስምሪት ፍቃድ ትነጠቃላችሁ መባላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የጎንደር ህዝብም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል የሀገር ባህል ልብስ እንዲለብስ ቤት ለቤት ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑም ታውቋል።