በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ የገባው የኮማንድ ፖስት ሃይል ከግቢው ተባረረ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 11/2010)በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ የገባው የኮማንድ ፖስት ሃይል በተማሪዎች ተቃውሞ እንዲወጣ ተደረገ።

ባለፈው ሳምንት በተማሪዎች የተጀመረውን የምግብ ማቆም አድማ ተከትሎ ወደ ግቢው የገባው የኮማንድ ፖስት ሃይል ዛሬ መውጣቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

አድማውን ለማስቆም የገባው ሃይል ተማሪዎችን የደበደበ ሲሆን 5 ተማሪዎች በደረሰባቸው ጉዳት ለከፍተኛ ህክምና ወደ ጅማ ተልከዋል።

በሌላ በኩል ከምስራቅ ጎጃም ወደ ትግራይ ክልል ተጭኖ ሊወሰድ የነበረው ብረት በነዋሪው በተወሰደ ርምጃ እንዲራገፍ ተደርጓል።

ከትላንት በስቲያ በምስራቅ ጎጃም መርጦ ለማርያም የሚገኘውን አሮጌ ድልድይ በማፍረስ ብረቱን በሶስት ተሽከርካሪዎች ጭነው ሊወጡ ሲሉ መታገታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች የተመታውን የምግብ አድማ ተከትሎ በኮማንድ ፖስቱ የሚታዘዙት የፌድራል ፖሊሶች ወደ ግቢው በመግባት በርካታ ተማሪዎችን ደብድበው ያስራሉ።

ይህ የኮማንድ ፖስቱ እርምጃ ያስቆጣቸው ተማሪዎች የታሰሩት እንዲፈቱ በመጠየቃቸው በድጋሚ ግቢውን የወረሩት የኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች ከፍተኛ ድብደባ በመፈጸማቸው አምስት ተማሪዎች ክፉኛ ተጎድተው ወደ ጂማና መቱ መወሰዳቸው ታውቅቋል።

የኮማንድ ፖስቱ የሃይል እርምጃ ይበልጥ ቁጣን በመፍጠሩ ተማሪዎች የታጠቁ ወታደሮች ከግቢያቸው እንዲወጡ የሚጠይቅ አዲስ ተቃውሞ ከሰኞ ጀምሮ በማካሄድ ላይ ናቸው።

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተቃውሞ እየበረታ መምጣቱን የተረዳው የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና የኮማንድ ፖስቱ አመራሮች ተማሪዎቹን ሰብስበው ማነጋገራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በስብሰባው የተገኙ ተማሪዎችም የኮማንድ ፖስት ወታደሮች ከግቢያችን ይውጡ  የሚል  ጥያቄ  አንስተዋል።

በግቢው ሰፍረው የሚገኙት ወታደሮች ተማሪዎችን እየደበደበ ለአካል ጉዳት የዳረገውና የስነልቦና ጫና እየፈጠረ በመሆኑ በአስቸኳይ ግቢውን ለቆ እንዲወጣ አለበለዚያ ተቃውሞአችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የተማሪዎቹ አቋምን የተገነዘቡት አመራሮችም በዩኒቨርሲቲው የሚገኘው ሃይል እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ወዲያውኑም የኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች ትጥቃቸውን ሰብስበው ከግቢው መውጣታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።

ተማሪዎቹ የታሰሩት ጓደኞቻቸው እስኪፈቱ በተቃውሞአቸው እንደሚቀጥሉ ማስታወቸውንም የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ወደ ትግራይ ክልል ተጭኖ ሊወሰድ የነበረው ብረት በነዋሪው በተወሰደ እርምጃ   እንዲራገፍ መደረጉ ተገለጸ።

ትላንት በምስራቅ ጎጃም መርጦ ለማርያም የሚገኘውን አሮጌ ድልድይ በማፍረስ ብረቱን ሶስት ተሽከርካሪዎች ጭነው ሊወጡ ሲሉ መታገታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ሌሊቱን ተሽከርካሪዎች እንዳይወጡ ጥበቃ ያደረገው የመርጦለማርያም ከተማ ነዋሪ በዛሬው ዕለት ወደ ትግራይ ሊወሰድ የነበረው ብረት ማስቀረታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የአከባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የአሮጌው ድልድይ ብረቶች በገበያ ላይ የሌሉ በጥንካሬአቸውም ተመራጭ ናቸው።

ለነዋሪው የደረሰው መረጃ በረቶቹን ጭነው ከከተማዋ ሊወጡ የተዘጋጁት ተሽከርካሪዎች መዳረሻቸው ትግራይ ክልል መሆኑን የሚገልጽ ነው።

ውስጥ ለውስጥ መረጃው ተዳርሶ ስለነበረ ተሽከርካሪዎቹ ከተማዋን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት በነዋሪው ታግተው እንዲቆሙ ተደርገዋል።

የአከባቢው የመንግስት ባለስልጣናትና ፖሊስ ተሽከርካሪዎቹን ሊያስለቅቋቸው ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም በነዋሪው ተቃውሞ ሊሳካ አልቻለም።

በመጨረሻም ከታገቱት ተሽከርካሪዎች ላይ የተጫነው ብረት ሙሉ በሙሉ እንዲቀርድ ተደርጎ በነዋሪው ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።