በኢትዮጵያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አድማ በማድረጋቸው በረራዎች ለሰዓታት ተስተጓጉለው ውለዋል።
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 09 ቀን 2010 ዓ/ም) የቢቢሲው የአዲስ አበባ ወኪል ኢማኑኤል ኢንጉዛ ከሥፍራው እንደዘገበው የአየር መንገዱ የአየር ትራፊክ ሠራተኞች ዛሬ ማለዳ ላይ አድማ በመምታታቸው የኬንያው ኬ ኪው ወደ ናይሮቢ የሚያደርገውን ጉዞ ጨምሮ የበርካታ አየር መንገዶች በረራ ለሰዓታት ተስተጓጉሏል።
የአየር ትራፊክ ሠራተኞቹ መሣሪያዎቻቸውን በማውረድ ማደማቸውን ያወሳው የቢቢሲው ዘጋቢ፣ የአመጻቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ለጊዜው አለመታወቁን ጠቅሷል።
እሱ ራሱ ጋዜጠኛው በአውሮፕላን ማረፊያው የደረሰው በኬንያ አየር መንገድ በበረራ ቁጥር ኬ ኪው 401 ወደ ናይሮቢ ለመጓዝ እንደነበር በማውሳት፣ ሆኖም አብራሪው መቼ በረራውን መጀመር እንዳለበት ግልጽ እንዳልሆነለት ለተጓዦች ለማስታወቅ መገደዱን ገልጿል።
በዚህም ሳቢያ ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ ሀገራት የሚደረጉ ጉዞዎች በመራዘማቸው ተጓዦች እየተጉላሉ ለመጠበቅ ተገደዋል።
በኢትዮጵያ የኢንደሥትሪ ሠራተኞች አድማ ብዙም ያልተለመደ መሆኑን ያወሳው ቢቢሲ፣የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ እንደሆነ ቢነገርም የድህነት ደረጃው በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና የሠራተኞች ደመወዝም ከሌሎች ሀገራት ጋር ሢነጻጸር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አትቷል።
ትናንት የንግዱ ማህበረሰብ ጋር የተገናኙት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዘርፉን ለማሻሻልና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ይበልጥ ለማሳደግ ቃል መግባታቸውንም የዜና ማሰራጫው ጠቅሷል።
በተለይ ሀገሪቱን ሚሊዮን ዶላር እያሳጧት ነው ያሉትን በውጭ ጉዞ ላይ የሚደረጉ ወጭዎችን በመቀነስ በኩል ተጨባጭ የማሻሻያ እርምጃዎችን እንደሚዎስዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ዶክተር አብይ በዚሁ ከባለሀብቶች ጋር ባደረጉት ውይይጥ ሀገሪቱ ስላጋጠማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማውሳታቸውን እና ሙስናን ስለመዋጋት አስፈላጊነት መናገራቸውን ቢቢሲ አመልክቷል።
በአፍሪካ በህዝብ ብዛቷ ሁለተኛ የሆነችው ሀገር ለንግዱ ማህበረሰብና ለባለሀብቶች ክፍት እንደሆነችም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።