የኢትዮ-ሶማሊ ክልል የአሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ቤተሰቦች ታሰሩ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 02 ቀን 2010 ዓ/ም) አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ጅግጅጋን ጎብኝተው በሄዱ ማግስት በአገዛዙ የተቋቋመውና በዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሄር የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የክልሉ ተጠሪ የሆኑት አቶ ጀማል ሙሃመድ ዋራፋ ቤተሰቦች ታስረው ምርመራ ተካሄድባቸው። ፓርላማው አቶ ጀማልን በቅርቡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ኮሚሽን አባል ሆነው እንዲሰሩ ሾሟቸው ነበር። አቶ ጀማል ሪፖርታቸውን ለፓርላማ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ በሄዱበት ወቅት፣ ቤተሰቦቻቸው በፕሬዚዳንቱ ልዩ ጥበቃ አዛዥ ኮሎኔል ሙስጣፋ ሳናርዬ ታፍነው ከተወሰዱ በሁዋላ ሰቆቃ ተፈጽሞባቸዋል። የአቶ ጀማል ባለቤት፣ ልጆቻቸውና እህቶቻቸው ታስረው ሰቆቃ ከተፈጸመባቸውና በቪዲዮ ከተቀረጹ በሁዋላ ዛሬ ጠዋት ተለቀዋል።
የህክምና ባለሙያ የሆኑት ወንድማቸው ዶ/ር ዲቅ ሞሃመድ ዋርፋሪ ታፍነው ወደ ማሰቃያ ቦታ ተወስደዋል። የክልሉ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር አብዲ ኢሌ የሚፈጽመውን ወንጀል እንዳያጋልጡ ለማስፈራራት የተወሰደ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።