በኢንቨስትመንት ሥም የኮንትሮባንድ ንግድ በትግራይ ተወላጅ ነጋዴዎች መስፋፋቱን ዶ/ር ደብረጺዮን አመኑ፣ የጋንቤላ የመሬት ወረራ ህገወጥ እንደነበር የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ጥናት አረጋገጠ

በኢንቨስትመንት ሥም የኮንትሮባንድ ንግድ በትግራይ ተወላጅ ነጋዴዎች መስፋፋቱን ዶ/ር ደብረጺዮን አመኑ፣ የጋንቤላ የመሬት ወረራ ህገወጥ እንደነበር የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ጥናት አረጋገጠ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 02 ቀን 2010 ዓ/ም) በኢንቨስትመንት ሥም ከፍተኛ የሆነ ማጭበርበር፣ ሌብነት፣ የኮንትሮባንድ ንግድ በትግራይ ተወላጅ ነጋዴዎች መስፋፋቱን ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል በማመን ጥፋተኞች ይጠየቃሉ ብለዋል።
ዶ/ር ደብረጺዮን ሁኔታው ሲገልጹም ”በህገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ይሳተፋሉ። ለምሳሌ የብረት ንግድ ሽያጭ ንግድን ማየት እንችላለን። አንድ ኮኮብ ያለው ሆቴል የሌለው ግለሰብ ከ30 እስከ 40 የሚደርስ የንግድ ፈቃድ ያወጣል። በዛ ፍቃድም በኢንቨስትመንት ሥም ካለቀረጥ ብረት ከውጭ አገር ያስገባሉ። እነዛው የትግራይ ነጋዴዎች ብረቱን ውስደው አማራና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይሸጡታል። ”ትግራይ ውስጥ የብረት ፋብረት ፋብሪካ አለ ወይ?” እስኪባል ድረስ በማጭበርበርና በሌብነት የትግራይ ሕዝብ መታወቅ ጀመረ።
በፊት በታታሪ ሰራተኝነት የትግራይ ሕዝብ ይታወቅ ነበር። አሁን ግን በነዚህ አጭበርባርዎች ምክንያት ሁለት ዓይነት ስሞች ወጡልን። ሃቀኛ ነጋዴዎችም በነሱ ምክንያት ሥማቸው ተበከለ። ክልላቸውን በድለው አገሩንም አበላሹት። እንደ በፊቱ ቢሆን አንጠልጥለ እንቀጣቸው ነበር። አሁንም እንቀጣቸዋለን።” ብለዋል። ዶ/ር ደብረጺዮን ነጋዴዎችን ከመውቀስ ውጪ የኮንትሮባንድ ንግዱ ዋነኛ አስተላላፊ ስለሆኑት የህወሃት ጄኔራሎችና ቤተሰቦቻቸው ገሃድ የወጣ ዘረፋ ግን ያሉት ነገር የለም።
በጋንቤላ ክልል የመሬት ወረራ ሙሉ ለሙሉ ሕገወጥ እንደነበር የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ጥናት አረጋግጧል። ይህንንም የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ ባለስልጣናት በጋንቤላ የብሄር ብሄረሰብ በዓል ላይ ተገኝተው መሬቱ በወረራ የተያዘ መሆኑን በማመን ምላሽ ሰጥተው ነበር። ይህን አስመልክቶ አስመልክቶም ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ ግዮን ሆቴል ውስጥ በተደረገው ስብሰባ ላይ ”እንደ ጋንቤላ የመሬት ወራሪዎች እንዳትሆኑ!” በማለት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን አንድ የትግራይ ተወላጅ ተናግረዋል። ሁሉንም ሌባ በማለት መውቀሳቸው በጥረታቸውና በላባቸው የሰሩትንም ደምረው መውቀሳቸው አግባብ እንዳል ነበር አውስተዋል።
ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ በበኩላቸው መሬቱ በወረራ መያዙን የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ጥናታዊ ሪፖርት ላይ መቅረቡን አስታውሰው ” ሁሉንም ሌቦች ማለት ግን አሳማኝ አለመሆኑን ገልጸዋል። ንግግራቸው ጥፋት ከሆነም በፓርቲያችን ይታያል ብለዋል።
አንድ ተሰብሳቢ በበኩላቸው ”ህወሃት ሁሌም አስቀድሞ አጥፍቻለሁ በማለት ሕዝቡ ችግሩን ከመናገሩ በፊት ይመጣል። እስከመቼ ተሃድሶ፣ ጥልቅ ተሃድሶ፣ እያላችሁ የክርስትና ሥም እየቀየራችሁ የምትመጡት?” ሲሉ ምክንያት በመደደር ችግሩ ይቀጥላል ብለዋል።