(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 21/2010)በመከላከያ ሰራዊት አባላት በሞያሌ ከተማ ስለተገደሉት ዜጎች እንዲያጣራ የተሰየመውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም የሚከታተለው መርማሪ ቡድን የማጣራት ተልዕኮውን እንዲያቋርጥ ታዘዘ።
በኢትዮጵያ ፓርላማ የተቋቋመው የስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቡድን ከመጋቢት 16 እስከ መጋቢት 24 ድረስ ወደ ሞያሌ ተጉዞ ምርመራ የማካሄድ እቅድ ነበረው።
ዋዜማ የቡድኑን አባል ጠቅሶ እንደዘገበው መርማሪ ቦርድ “ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ” ነው በሚል ተልዕኳቸውን አቋርጠው እንዲመለሱ ተደርጓል።
አስራሁለት አባላትን ያካተተውና በፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አፈጻጸሙን እንዲያጣራ የተቋቋመው መርማሪ ቡርድ አባላት መጋቢት 16 ወደ ሞያሌ ለመጓዝ ተሰባስበው ነበር።
ይሁንና አንድ የቡድኑ አባል ለዋዜማ እንደገለጹት “ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ” ነው በሚል ከጉዟቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
የቡድኑ አባል “የተወሰነው ጉዞውን መቀጠል አለብን፣አንመለስም”ቢልም ሌሎች ደግሞ መመለስ አለብን ስላሉ ጉዞው ሳይካሄድ ቀርቷል ብለዋል።
መርማሪ ቡድኑ ጉዞውን እንዲያቋርጥ የትኛው ባለስልጣን ትዕዛዝ እንደሰጠ እንደማያውቁ መናገራቸውም ነው የተገለጸው።
በፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያጣራ የተቋቋመው አጣሪ ቡድን ወደ ሞያሌ ተጉዞ ከሟች ቤተሰቦች፣ከቁስለኞችና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመነጋገርና መረጃ በማሰባሰብ በመከላከያ ሰራዊቱ ስለተገደሉት ዜጎች አጣርቶ ለመምጣት ተልዕኮ ነበረው።
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በሞያሌ ከተማ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በመረጃ ስህተት ነው በሚል ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለው አስራሶስት ሰዎች ቆስለዋል።
ቀይ መስቀል እንደሚለው ደግሞ ከ10ሺ በላይ ሰዎች ወደ ኬንያ ተሰደዋል።
ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ማስቆጣቱም ይታወሳል።
አገዛዙም ግድያውን የፈጸሙትን የሰራዊቱን አባላት ትጥቅ አስፈትቶ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጾ ነበር።እነማን እንደሆኑ እና የት እንደታሰሩ እስከአሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።
አገዛዙ የሰራዊቱ አባላት ድርጊቱን የፈጸሙት የኦነግ ታጣቂዎች ወደ አካባቢው ገብተዋል በሚል ሰበብ እንደሆነ ሲገለጽም ቆይቷል።
ብዙዎች ግን በከተማ ውስጥ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ቦታ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ያገኙትን ሁሉ ሲገድሉ እንደነበር ምስክርነታቸውን መስጠታቸው አይዘነጋም።