የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ተጠራ

 (ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 20/2010) እነእስክንድር ነጋ እንዲፈቱ ግፊት ለማድረግ የታሰበ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ለነገ ተጠራ።

በሀገር ቤትና በውጭ የሚገኙ አክቲቪስቶች ያዘጋጁት የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ባለፈው ዕሁድ የታሰሩት ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎችን በተመለከተ ትኩረት እንዲያገኙና በአገዛዙ ላይ ጫና በመፍጠር እንዲፈቱ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

ኮከብ የሌለበትን ሰንደቅ ዓላማ ይዛችኋል በሚል በፖሊስ የታሰሩት እነእስክንድር ነጋ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በኮማንድ ፖስቱ የሚፈለጉ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ።

እስክንድር ነጋን ጨምሮ 12 ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር አምስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል።

ስለጀግኖቻችን ዝም አንልም የህዝብ ልጆችን ልቀቁ በሚል መሪ ቃል ነገ ዓርብ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚደረገው ዘመቻም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው የታሰበ መሆኑን አዘጋጆቹ ይናገራሉ።

በማህበራዊ ሚዲያዎች የተበተነው ዘመቻ ላይ እንደተገለጸው እነእስክንደር የታሰሩበት ሁኔታ ለጤናቸው አደገኛ ነው።

በጠባብ ክፍል ከ90 በላይ ሆነው የታሰሩት ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ከየአቅጣጫው ግፊቱ በጨመረበት በዚህን ወቅት ጉዳዩ በኮማንድ ፖስቱ የተያዘ መሆኑ ተገልጿል።

ነገ በቲውተር ፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚደረገው ዘመቻ እነእስክንድር የሚገኙበትን ሁኔታ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ በአገዛዙ ላይ ጫናና ግፊት እንዲፈጠር ለማድረግ የታሰበ ነው።

በዘመቻው የተለያዩ መልዕክቶች የሚተላለፉ ሲሆን በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በሰብዓዊ መብት ጥሰት አንጻር እየፈጸማቸው ያሉ ተግባራት የሚገለጹበት ይሆናል ተብሏል።

በመልዕክቶቹም የታሰሩት እያንዳንዳቸው በፎቶግራፍ ከስማቸውና ከደረሰባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር እየተገለጸ የሚተላልፍ ይሆናል።

አሁን ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ጫና እንዲያደርግ የሚጠይቁ መልዕክቶችም ይተላለፋሉ ተብሎ ታቅዷል።

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተሳትፎ ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ለዘመቻው መሳካት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

ባለፈው ዕሁድ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መኖሪያ ቤት በተደረገ ፕሮግራም የታደሙትን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎች በፖሊስ ታስረው ክስ ሳይመሰረትባቸው በስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል።

ኮከብ የሌለበትን ሰንደቅ ዓላማ ይዛችኋል በሚል የታሰሩት እነዚህ ግለሰቦች በኮማንድ ፖስቱ ጉዳያቸው እንደሚታይ መጠቀሱ እስሩ የታሰበበት ሊሆን እንደሚችል ነው ታዛቢዎች የሚገልጹት።

ያልተፈቀደ ስብሰባ አድርጋችኋላ የሚል ክስም እየተሰማ ነው።

በተለይም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌ በቅርቡ በወልዲያና በሌሎች አከባቢዎች ያደርጓቸውን ጉብኝቶች በማንሳት ጥያቄ እንደቀረበባቸው ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።