(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13/2010)በኦሮሚያ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገበ።
የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም በራሱ በኦሮሚያ ክልል መገናኛ ብዙሃን ላይ ተጽእኖ ማድረጉም ተመልክቷል።
ኢንተርኔት ፍለጋ ከአዳማ አዲስ አበባ የሚመላለሱ ግለሰቦችም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከፍተኛ የሰራዊት ሃይል የተሰማራበት የኦሮሚያ ክልል ከሌሎች ክልሎች በተለየ የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠበት ምክንያት አልታወቀም።
የኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ ኦ ቢ ኤን እንደዘገበውም መንግስታዊው ኢትዮ ቴሌኮም ስርጭቱ ስለተቋረጠበት ምክንያት የሰጠው ምክንያት የለም።
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የኢትዮ-ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ ከያዙ በኋላ ስልካቸውን ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆን ኢንተርኔቱ የተቋረጠበትን ምክንያት ሳይገልጹ ቀርተዋል።
በኢንተርኔት መቋረጥ ሳቢያ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ መቸገሩን የኮሌጁ ሃላፊዎችና ተማሪዎች አስታውቀዋል።
ራሱ ኦ ቢ ኤን በኢንተርኔት መስተጓጎል ሳቢያ ፕሮግራሙን በአግባቡ ለማካሄድ መቸገሩን አስታውቋል።
ግለሰቦችና ድርጅቶችም በኢንተርኔት መቋረጥ ሳቢያ በገቢያቸውና በስራ እንቅስቃሴያቸው ላይ ያደረሰውን ተጽእኖ በምሬት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
አንድ አስተያየት ሰጪ ለስራው ኢንተርኔት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ከአዳማ አዲስ አበባ እየተመላለሰ ኢንተርኔት ለመጠቀም መገደዱን ገልጿል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ተከትሎ በሞያሌ 13 ያህል ሰላማዊ ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት መገደላቸው ሲታወስ መንግስት በስህተት ነው የገደልኳቸው በማለት ይቅርታ መጠየቁ አይዘነጋም።
በባሌ ዞን በሰዌና ወረዳ ቡርቃ ጠሬ በተባለ መንደር ሶስት ሕጻናትን ጨምሮ
የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 5 ሰዎች ባለፈው አርብ በሶማሌ ልዩ ሃይል መገደላቸው ይታወሳል።
ልዩ ሃይሉም በኮማንድ ፖስቱ እዝ ስር መሆኑንም ኮማንድ ፖስቱ መግለጹ አይዘነጋም።
በኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች በደፈጣ በሚሰነዝሩት ጥቃት በመከላከያ ሰራዊት አባላትና ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸው በመነገር ላይ ነው።
ከኦሮሚያ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመታፈስ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በተለይ በወለጋ እስራቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው መረጃዎች ያመለከቱት።