ከፍተኛ የመድሃኒት እጥረት ተከሰተ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13/2010)በኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ከፍተኛ የመድሃኒት እጥረት በመከሰቱ ሕሙማን ሕይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ።

ፋይል

አቅራቢዎችም ሆነ የጤና ተቋማት በመድሃኒት እጥረት ምክንያት አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን አስታውቀዋል።

በተለይም የስኳርና የልብ ሕሙማን ሕይወታቸው አደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ከ330 በላይ መድሃኒት አስመጪዎች ቢገኙም በውጭ ምንዛሪ መታጣት ምክንያት ስራቸውን በአግባቡ እየሰሩ አይደሉም።

በዚሁም ሳቢያ የመንግስትም ሆነ የግል መድሃኒት ቤቶች ከፍተኛ እጠረት እንደገጠማቸው ነው የተነገረው።

በዚሁም ሳቢያ ሕሙማን የሚፈልጉትን መድሃኒት በሃገር ውስጥ ማግኘት ባለመቻላቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ኢ ኤን ኤን የተባለው የገዥው ፓርቲ ልሳን የሆነው ቴሌቪዥን እንደዘገበው በተለይ የልብና የስኳር ሕሙማን በመድሃኒት እጥረቱ ምክንያት ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል።

ይህንኑ በተመለከተ የመድሃኒት ቤት ሰራተኞች ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በሃገሪቱ ባለው የመድሃኒት እጥረት የሪፈራል ሆስፒታል የሆነው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልም ችግር ላይ መሆኑ ታውቋል።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረሕይወት እጥረቱ ትልቅ ችግር መፍጠሩን ነው የተናገሩት።

የሕክምና መገልገያ አስመጪዎች ማህበር ሰብሳቢ አቶ አብነት ድንበሩ በበኩላቸው ለመድሃኒት እጥረቱ ዋነኛ ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ያለው የመድሃኒት ክምችት እየተመናመነ በመሆኑ በቀጣዮቹ ወራት በሃገሪቱ በችግሩ ሳቢያ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ የሕክምና ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ።