በሰሜን ወሎ ሮቢት ከተማ ላይ አንድ አውቶቡስ በድንጋይ ተመታ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 13 ቀን 2010 ዓ/ም) የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት ዛሬ ጠዋት ከአዲስ አበባ የተነሳ ስካይ ባስ በሚል የሚጠራ የመንገደኞች ማመላለሻ አውቶቢስ ሮቢት ከተማ ላይ በድንጋይ ተመትቶ የሚከናው መስታውት መሰባባሩን ገልጸዋል።
ወጣቶቹ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ በተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት ይድረስ አይድረስ የታወቀ ነገር የለም። ጥቃቱ እንደተሰነዘረ ከቆቦ የተነሱ ወታደሮች ወዲያውኑ አካባቢውን ተቆታጥረውታል። በቅርቡ በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ተነስቶ የነበረውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ በርካታ ወጣቶች ታስረው የተወሰኑት ሲፈቱ ሌሎች ደግሞ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል። ምንም እንኳ አሁንም አካባቢው በወታደሮች እየተጠበቀ ቢሆንም ወጣቶች አልፎ አልፎ የተለያዩ ጥቃቶችን ይፈጽማሉ። የዛሬውም ጥቃት የዚሁ የተቃውሞው አንድ አካል መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ በአመራር ላይ የሚያደርገው የሰው መቀያየር በሃገሪቱ ላይ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ እንደማይሆን የክልሉ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትር ሊሾም እንደሆነ የሚነገረው ነገር ለአገሪቱ ችግር “በዘላቂ ፍትሄነት” እንደማያገለግል የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ በየአካባቢው የተከሰተውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ገዥው መንግስት ቁልፉን ሊከፍት ይገባል ይላሉ።
ብዙውን ጊዜ አገዛዙ በህዝብ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን የማዳፈን ሩጫ ሲያደርግ እንጅ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ሲጥር እንዳይደለ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች ፤ የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ በእጁ ስለሆነ ፈጥኖ ወደ መፍትሄ ይገባ ዘንድ አሳስበዋል፡፡
በየጊዜው በህዝብ ንቅናቄ ዘንድ የሚከሰቱ ጥያቄዎችን ምላሽ የሚሰጠው አንድም በጉልበት ሌላ ጊዜም በፖለቲካዊ ውሸት መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ። ገዥው መንግስት በእጁ የያዘውን ቁልፍ ለሚሰራ አካል ማስረከቡ አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ፣ ይህን መፈጸም ካልተቻለ ጉዳቱ በገዥው መንግስትና በህዝቡ ላይ ሊወድቅ ይችላል ይላሉ።