በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የኢትዮጵያው ወላይታ ዲቻ ከግምት ውጪ የግብጹን ዛማሊክ አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አላፊ ቡድን ሆነ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ/ም) የግብጹ አንጋፋ ቡድን ዛማሌክና የኢትዮጵያው ወላይታ ዲቻ በመዲናዋ ካይሮ 2 ሽህ ተመልካቾች በተገኙበት አል-ሰላም መጫወቻ ሜዳ ባደረጉት ጫወታ በመደበኛ የጫወታ ክፍለ ጊዜ ዛማሌክ 2-1 ቢያሸንፍም በተመሳሳይ ውጤት ወላይታ ዲቻ 2-1 በማሸነፉ 3-3 አቻ ሆኑ። አሸናፊውን ቡድን ለመለየት በተሰጠው ፍጹም ቅጣት ምት የዛማሌኮቹ አይመን ሄፍኒ እና መሀመድ አብዱልአዚዝ የተሰጣቸውን ፍጹም ቅጣት ምት በመሳታቸው ወላይታ ዲቻ በአጠቃላይ ውጤት 4-3 አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።
ዛማሌክ የአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫን ለአምስት ጊዜያት መሳም የቻለ ውጤታማ ቡድን ነው። በግብጽ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዛማሌክ 10 ነጥብ 30 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የሚያወጣ ሲሆን ከአፍሪካ ሃብታም ቡድኖች ውስጥ በስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የዛማሌክን ሽንፈት አስመልክቶ የግብጽ ብዙሃን መገናኛዎችና ታዋቂ ሰዎች በሽንፈቱ ዙሪያ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። የቀድሞው የዛማሌክና የግብጽ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረው አህመድ ሆሳም ሚዶ ነውረኛ አስተያየት ከሰጡት ውስጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ”ከወላይታ ዲቻ ተጫዋች ውስጥ ለግብጽ ሶስተኛ ዲቪዚዮን ተሰልፎ ለመጫወት የሚመጥን አንድም ተጫዋች የላቸውም። የዛማሌክ ተሰላፊዎች አሳፋሪዎች ናቸው።” ሲል
ሚዶ ለወላይታ ዲቻ ያለውን ዝቅተኛ ግምት በዓደባባይ ተናግሯል።
ለሩሲያው 2018 የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክለው ከቀረቡት አምስት አገሮች አንዷ የሆነችው ግብጽ ከዓለም 44ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 5 ደረጃ ላይ ስትገኝ ኢትይዮጵያ በበኩሏ ከዓለም 137ኛ በአፍሪካ ደግሞ 39ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የወላይታ ዲቻ ቡድን ድልን አስመልክቶ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በማኅበራዊ ድረገጾች ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ዲቻ ማለት በወላይተኛ እና በጋሞኛ ቋንቋዎች ትርጉሙ እድገት ማለት ነው።