ከ51 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት በአደንዛዥ እጽ ተጠቅቷል ተባለ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 07 ቀን 2010 ዓ/ም) ዲኬቲ ኢትዮጵያ ባዘጋጀው የወጣቶችና የስነ ተዋልዶ የምክክር ዝግጅት ላይ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛሃኞቹ ወጣቶች በአደንዛዥ ሱሶች ተጠቂ መሆናቸውንና ራስን የማጥፋት እርምጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ10 እስከ 24 ዓመት ከሚሆናቸው ወጣቶች ውስጥ 51 ከመቶ ያህሉ ጫት ቃሚዎች፣ 45.6 ከመቶ የሚሆኑት የአልኮል መጠጥ ጠጪዎች፣ 4.4 ከመቶ የሚሆኑት ሲጋራና ሌላ ነገሮች እንደሚያጨሱ ጥናቶች አረጋግጠዋል። ጫት ከሚቅሙት መካከል 56.6 ከመቶዎቹ ወንዶች፣ 36.6 በመቶዎቹ ደግሞ ሴቶች ናቸው።
በፓዝ ፋይንደር የወጣቶችና የጤና ልማት ፕሮግራም አማካሪ የሆኑት ሲስተር ወርቅነሽ ቀሬታ እንዳሉት፣ አብዛሃኞቹ ወጣቶች ሕይወታቸውን የሚያጡት በአደጋ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ራስን ማጥፋት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ። ከዩንቨርሲቲዎች ጀምሮ እራስን ማጥፋት በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቷልም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከጫት በተጨማሪ ሺሻና አደንዛዥ የሆኑ ማሪዋናዎች ይሸጣሉ። አንዳንድ ዩንቨርሲቲ ውስጥ እጾችን በሃይላንድ እያበቀሉ ይሸጣሉ። ማሪዋና እየተወቀጠ ጠላ ውስጥ እየተጨመረ ይሸጣል። ማሪዋና ቅርብ በሚሆን መልኩ ለታዳጊና ወጣቶች እንዲደርሳቸው እየተደረገ መሆኑንና አስፈሪ ደረጃ ላይ መድረሱን ሲስተር ወርቅነሽ ገልጸዋል።
በሴቶች ላይ በተደረገው የስነ ተዋልዶ ጥናት አሁንም 40 ከመቶ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች የሚሆናቸው ወጣት ሴቶች ጋብቻ ይፈጽማሉ። ከነዚህ ውስጥ 20 በቶዎቹ ከ15 ዓመት በታች ናቸው። ከ100 ወጣት ሴቶች ውስጥ 13ቱ ያልተፈለገ እርግዝና ያጋጥማቸዋል። በአሁኑ ሰዓት የወሲብ መጀመሪያ እድሜ 16 ዓመት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የገጠር ልጆች ቀድመው ወሲብ ይፈጽማሉ።
45 በመቶ የሚሆኑ የአማራ ክልል ልጃገረዶች ከ18 ዓመት በታች ሆነው ጋብቻ ይፈጽማሉ። በአገሪቱ የፈለገው ዓይነት ሕግ ቢወጣም አፈጻጸም ስለሌለው ችግሩን እንደማይፈታው ሲስተር ወርቅነሽ መግለጻቸውን ሸገር ኤፍኤም ዘግቧል።