ሼክ ሙሃመድ ሁሴን አላሙዲን የታሰሩበት ቦታ እንደማይታወቅ ተገለጸ

ሼክ ሙሃመድ ሁሴን አላሙዲን የታሰሩበት ቦታ እንደማይታወቅ ተገለጸ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 07 ቀን 2010 ዓ/ም) ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ይዞት በወጣው ሰፊ ዘገባ ከአላሙዲን ጋር አብረው ታስረው ልኡላንና ባለሀብቶች ከእስር ሲፈቱ አላሙዲን ግን እስካሁን አልተፈቱም።
የአላሙዲን የፕሬስ ክፍል ፣ ባለሃብቱ ሪትዝ ካርልቶን በሚባለው ሆቴል ታስረው ከቆዩ በሁዋላ ወደ ሌላ ሆቴል መዘዋወራቸውን ቤተሰቦቹ ቢናገሩም፣ የታሰሩበትን ቦታ እንደማያውቁ አስታውቋል። ከቤተሰቦቻቸው ጋር በየጊዜው እንደሚገናኙና ደህና መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።
አላሙዲ ከሌሎች ባለሃብቶች በተለየ በእስር እንዲቆዩ የተደረገው ምናልባትም በመላው አለም ከፈጠሩት የንግድ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ጋዜጣው ግምቱን አስፍሯል። አላሙዲን ከቀድሞው የሳውድ አረቢያ ንጉስ አብዱላህ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደነበራቸው እና ንጉሱ በኢትዮጵያ የሚገኘውን የሳውዲ ስታር የእርሻ ስራ ይደግፉ እንደነበር የዘገበው ጋዜጣው፣ አዲሱ የሳውዲ መንግስትም በፕሮጀክቱ ዙሪያ ፍላጎት አሳይቶ ነበር።
ሼክ አላሙዲን በጉልምስና እድሜያቸው ወደ ሳውዲ አረቢያ ካመሩ በሁዋላ፣ ታዋቂ ከሚባሉ ሰዎችና የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የጥቅም መረብ ዘርግተዋል። በተለይም ከ7 ዓመታት በፊት ህይወታቸው ካለፈው መከላከያ ሚኒስትርና አልጋ ወራሽ ከነበሩት ከልኡል ሱልጣን ቢን አብዱላዚዝ ጋር የጠበቀ የንግድ ግንኙነት በመፍጠር ፣ የልኡሉን ገንዘብና ስልጣን መከታ በማድረግ ስራቸውን እንዳስፋፉ ጋዜጣው ዘግቧል።
አላሙዲ ከ30 ዓመታት በፊት ሚድሮክን እንደመሰረቱ የሳውድ አረቢያን የመሬት ውስጥ የጋዝ ማጠራቀሚያ ግንባታን ለመስራት በቢሊዮን የሚቆጠር የኮንትራት ስምምነት ተፈራርመዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የአለም ክፍሎች የንግድ ስራዎችን እየሰሩ ሃብታቸውን አስፋፍተዋል።
አላሙዲ ለክሊንተን ፋውንዴሽን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር መስጠታቸው፣ ከመስከረም 11፣ 2001 በኒዮርክ ከተፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃት 3 አመት በሁዋላ ደግሞ አለማቀፍ ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ከአሜሪካውያን ጋር እንዲተዋወቁ እንዳደረጋቸው የዘገበው ጋዜጣው፣ በኢትዮጵያም አወዛጋቢ ስብዕና ያላቸው ሰው መሆናቸውን ጠቅሷል።
ከገዢው ፓርቲ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸውና ድርጅቱን በገሃድ የሚደግፉት አላሙዲን፣ በዚህ የተነሳ አገዛዙን በሚቃወሙት ዘንድ እንዲጠሉ አድርጓቸዋል። በተቃራኒው የአገዛዙ ሰዎች አላሙዲን እንዲፈቱ እንደሚፈልጉ በዘገባው አስፍሯል።