ታህሳስ 13 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ፕሬዝዳንት በመሆን በጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፓርቲውን የሚመሩ አስር አባላት ያሉትን የካቢኔ አባላት ቅዳሜ እንደሚያቀርቡ አስታወቁ።
ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፤አዲሱ ፕሬዚዳንት ነገ ታህሳስ 14 ቀን በሚካሄደው የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ፓርቲውን የሚመሩ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት (ካቢኔ) መርጠው በመለየት ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ያቀርባሉ።
ከዚህ ጎን ለጎን በዕለቱ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሰብሳቢና ዋና ፀሐፊ እንዲሁም የኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት መረጣ እንደሚካሄድም ዶክተር ነጋሶ ገልጸዋል።
ፓርቲውን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ለመምራት የተመረጡት ዶ/ር ነጋሶ በአመራር ዘመናቸው በስድስት ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
እነዚህም አበይት እቅዶቻቸው፦ በፓርቲው ፕሮግራምና ስትራቴጂክ ሰነድ ውስጥ የተካተቱትን ዓላማዎች ማሳካት፣ የፓርቲውን ውስጣዊ ድርጅትን በሰው ኃይልና በገንዘብ ማጠናከር፣ ፓርቲው እስካሁን ወደ ሕዝብ በስፋት ያልሄደ በመሆኑ ወደ ሕዝቡ በስፋት እንዲወርድ ማድረግ፣ የሕግና ሰብአዊ መብት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴን በማጠናከር በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ለታሰሩ አባላት ልዩ ትኩረት መስጠት፣ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት መፍጠር እና በመጪው ዓመት ለአዲስ አበባ አስተዳደር በሚካሄደው ምርጫ ላይ ዝግጅት ማድረግ እንደሆኑ አብራርተዋል-
አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ከተቋቋመ በኋላም፤በውጪ ግንኙነት በኩል ፓርቲውን ይበልጥ በማጠናከር-ውጪ አገር ከሚገኙ የፓርቲው ደጋፊዎችና ኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኝቶ መነጋገርም በእቅዳቸው የተያዘ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከኢህአዴግ ጋር የሚደረገው ድርድር በአንድነት ፓርቲ በኩል ለድርድር በሩ ክፍት ቢሆንም፤ ከኢህአዴግ በኩል ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለ የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ፤ በዲፕሎማሲው ካምፕ በኩል ከምርጫው በኋላ ተዳክሞ የነበረው ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በተለይ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የድርጅቱ አንዳንድ አመራሮች እንዲታሰሩ መደረጉና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቀርበው ኃይለ ቃል የተሞላበት ንግግር ካደረጉ እና “አኬልዳማ” የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሕዝብ ከቀረበ በኋላ 14 አገራት አባል የሆኑበት የለጋሾች ቡድን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ መከታተል መጀመሩን ዶ/ር ነጋሶ ጨምረው ገልፀዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አባላት ፓርቲያቸውን እየተወ ወደ አንድነት ስለሚገቡበት ሁኔታ የተጠየቁት ዶ/ር ነጋሶ ፦” በግል የሚመጡት በድርጅታችን ሕገ-ደንብ መሠረት ሂደቱን እያጠናቀቁ አባል ይሆናሉ። በሕገ-መንግስቱ የመደራጀት ነፃነት መብት መሠረት ዜጎች በመሰላቸውና ይበጀናል ከሚሉት አካል ጋር መደራጀት ይችላሉ” ሲሉ መልሰዋል።
ዶክተር ነጋሶ አንድነት ፓርቲን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ሲመረጡ የፖለቲካ ምህዳሩ በተበላሸበት አገር አንድን ፓርቲ ለመምራት መመረጥ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል በመጥቀስ፤ ሆኖም የተሰጣቸውን ሀላፊነት የተቀበሉት የህይወት መስዋዕትነት እስከመክፈል ድረስ ዝግጁነት ስላላቸው እንደሆነ ማስታወቃቸው ይታወሳል።