የፍትህ ጋዜጣ ቢሮ እና የዋና አዘጋጁ ቤት አሁንም በደህንነት ሀይሎች እንደተከበበ ነው

13 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የደህንነት ሀይሎች ከትናንት በስቲያ ከቀኑ 5 ሰአት ጀምሮ የፍትህን ቢሮ እና የዋና አዘጋጁን የተመስገን ደሳለኝን መኖሪያ ቤት መክበባቸው ታውቋል

የአዘጋጁን የሀይለመስቀል ባሸዋምየለህን ስልክ ሲም ካርድ አውጥተው በመውሰድና ማንነቱን የሚያንቋሽሽ ስድብ ከመስደብ ውጭ ፣ የደህንነት ሰራተኞቹ ጋዜጠኞችን ለማሰርም ሆነ ለመደብደብ ሙከራ አላደረጉም።

ይሁን እንጅ ጋዜጠኞቹ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና የደረሰባቸው በመሆኑ ስራቸውን ተረጋግተው ለመስራት አልቻሉም።

“የመለስ ደህንነቶች ምን እንደሚያደርጉ አናውቅም፣ ብቻ የማፊያ ስራ ሲሰሩ እያየናቸው ነው” ሲል አንድ ስሙን ለመግለጥ ያልፈለገ ጋዜጠኛ ለኢሳት ተናግሯል።

አውራምባ ጋዜጣ መዘጋቱዋን ተከትሎ ፍትህ  በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት የሚያቀርብ ብቸኛ ጋዜጣ ነው።

የፍትህ አምደኛ የነበረው ታዋቂው ብእረኛ አቤ ቶክቼው በቅርቡ ከደህንነት ሀይሎች በተሰነዘረበት ማስፈራሪያ አገር ጥሎ መሰደዱ ይታወቃል።

ፍትህ ጋዜጣ በእየሳምንቱ በሚያቀርበው ጠንካራ ትችት ከፍተኛ ተነባቢ ጋዜጣ ሆኖ ለመውጣት መቻሉ ይነገራል።

አቶ ሽመልስ ከማል የጋዜጣውን አዘጋጆች ወደ መስሪያቤታቸው እየጠሩ ሲያስጠነቅቁዋቸው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የስዊድን ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ተከትሎ በመለስ መንግስት ላይ የሚደረገው አለማቀፍ ጫና እየጨመረ ነው።

የጀርመን መንግስት የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ተበላሽቶአል በሚል ምክንያት ለአገሪቱ ሊሰጠው የነበረውን 14 ሚሊዮን ዩሮ አግዷል።

ይህ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ እርምጃ የመለስ መንግስት በአውሮፓ እና በአውሮፓ ህብረት ጠንካራ አጋር ከሆነው የጀርመን መንግስትን ጋር ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱን አመላክቷል።

በተመሳሳኢ ዜናም ታዋቂ አሜሪካዊያን እስክንድር ነጋ እንዲፈታ እና  ለመለስ መንግስት የሚሰጠው እርዳታም እንደገና እንዲጤን ጠይቀዋል።

የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዊሊያም ኢስተርሌይ፣ የናሽናል ፐሬስ ክለብ ፕሬዚዳንት ማርክ ሀምሪክ፣ የኦፕን ሶሳይቲ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት አርየህ ኒየር ፣ የሂውማን ራይትስ ወች ዋና ዳይሬክትር ኬኒዝ ሮዝ እና የሲፒጄ ዋና ዳይሬክተር በጋራ በመሆን በኒው ዮርክ ቡክ ሪቪው ጆርናል ላይ ባወጡት ደብዳቤ ” እስክንድር ነጋ የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች በህዝቡ ላይ የሚፈጽሙትን ጭቆና፣ ስቃይ፣ እና የመብት አፈና እንዲያቆሙ በመጠየቁ መታሰሩን አውሰተዋል።

እስክንድር በአሜሪካ ያደገ እና የአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ እንዳለው ቢታወቅም ስደትን አለመምረጡ ለዲሞክራሲ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል የሚሉት ጸሀፊዎች፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑት ምእራባዊያን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማፈን የምትጠቀምበትን የሽብርተኝነት ህግ እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።

በተለይ የስቴት ዲፓርትመንት ዋና ጸሀፊ የሆኑት ሂላሪ ክሊንተን ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ፣ ለኢትዮጵያ በእየአመቱ የምንሰጠው 600 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጭቆናን ለማስፋፋት እየዋላ አለመሆኑን እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።