(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 4/2010) የምርት ገበያ በሁለት ወር ውስጥ ብቻ የግብይት መጠኑ በ40 ሺ ቶን ቀነሰ።
በሃገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ለግብይቱ መቀነስ ዋነኛ ምክንያት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት የየካቲት የግብይት አፈጻጸም የሚያሳየው ሪፖርት እንዳመለከተው የግብይት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መሄዱን የምርት ገበያ መረጃዎች አመልክተዋል።
በየካቲት ወር የነበረው ግብይት ካለፈው ጥር ጋር ሲነጻጸር 28 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
የየካቲት ወር ግብይት በታህሳስ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ደግሞ ከ105ሺ ቶን ወደ 66 ሺ ቶን የቀነሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይህም 38 በመቶ ቅናሽ የታየበት ሆኗል።
የግብይት መጠኑ በገንዘብ ሲተመን የየካቲት ወሩ ከታህሳስ ጋር ሲነጻጸር ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ቅናሽ የታየበት ሆኗል።
ይህም ካለፉት ሶስት ተከታታይ ወራት የገንዘብ አፈጻጸም አንጻር እያሽቆለቆለ መሄዱን የሚያመላክት ነው።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለግብይት ከሚያቀርባቸው ቡና፣ሰሊጥና ቦለቄን ከመሳሰሉት ምርቶች የቡና እና ሰሊጥ ከፍተኛ ቅናሽ ታይቶባቸዋል።
በሃገር ውስጥ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ከምርት ገበያ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት የግብይት አፈጻጸሙ እያሽቆለቆለ ለመሄዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው በሃገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ እንደሆነም ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የደቡብና የኦሮሚያ ክልል ቡና አቅራቢዎች ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የባንክ እዳ እንዲሰረዝላቸው መንግስትን በደብዳቤ መጠየቃቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።
የደቡብና የኦሮሚያ ክልል የቡና አጣቢዎች፣አበጣሪዎችና አቅራቢዎች የዘርፍ ማህበር ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ለንግድ ባንክና ለክልል መንግስታት በጻፈው ደብዳቤ “የቡና አምራች አርሶ አደርና በቡና ንግድ ስራ ላይ የተሰማራው አቅራቢና ቡና ላኪ የኢሕአዴግ መንግስት በተከተለው የተሳሳተ የቡና ፖሊሲ ምክንያት ኪሳራ ላይ ወድቀናል” ብሏል።
መንግስት የተከተለው ፖሊሲ አርሶ አደሩ በኤክስቴንሽን እንዳይደገፍ፣ቡና በምርጥ ዘር እንዳይታገዝና የበሽታና ምርምር ስራ እንዳይኖር ማድረጉን በደብዳቤው ጠቅሷል።