ታህሳስ 12 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመንግስት ላይ የሚያደርጉት ተቃውሞ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ መንግስት ስደተኞችን በማስፈራራት ድጋፍ ለማግኘት እየሞከረ ነው ተባለ
የመለስ መንግስት በፖለቲካው መስክ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ የተባሉ ስደተኞችን ሰነድ ለመንግስታት የውጭ አገር መስሪያቤቶች በመላክ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ለማድረግ አዲስ ስልት ቀይሷል።
በጀርመን አገር አከን ከተማ ነዋሪ የሆነው ነብዩ አለማየሁ ላለፉት 10 አመታት በድረገጾች ላይ ጽሁፎችን በማቅረብ ታዋቂነትን ማትረፉ ያበሳጨው የመለስ መንግስት፣ ስደተኛውን ለማሸማቀቅ የግለሰቡን ሰነድ ለጀርምን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳልፎ ሰጥቷል።
የጀርመን መንግስት ግለሰቡ ወደ ኢትዮጵያ ቢመለስ ምንም እንደማይሆንና እንክብካቤ እንደሚደረግለት በመግለጥ፣ ግለሰቡ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ ታውቋል።
ነብዩ እርሱን በተመለከተ በትምህርት ስም በውጭ የሚላኩት የህወሀት አባላት መረጃዎችን ለኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰጥተዋል ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል
በአሁኑ ጊዜ በህክምና ላይ የሚገኘው ነብዩ፣ የጀርመን መንግስት የስደተኝነት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ ከአገር የሚያስወጣው ከሆነ ፣ በህይወቱ ላይ አደጋ ሊያደርሱበት እንደሚችሉ ተናግሯል
ነብዩ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲረዱትም ጥሪ አቅርቧል።
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በቅርቡ አዲስ የዲያስፖራ ፖሊሲ መቅረጹ ይታወቃል።
ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉትን የጀርመን ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።