(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 15/2010)
እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በዛሬው እለት ከወህኒ ተለቀቁ።ከሚያዚያ 2001 ጀምሮ ላለፉት 9 አመታት በቃሊቲና በዝዋይ ወህኒ ቤት በእስር ላይ የቆዩት እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ዛሬ ከዝዋይ ወህኒ ቤት መውጣታቸው ተረጋግጧል።
ከብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ እና ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር ዛሬ ከወህኒ የወጡት መኮንኖች እና ሌሎች እስረኞች ኢንጂነር መንግስቱ አበበ፣ኮሎኔል አበረ አሰፋ፣ኮሎኔል ሰለሞን አሻግሬ፣ሻለቃ መኮንን ወርቁ፣ሻለቃ መሰከረ ካሳ፣ሻለቃ ምስጋናው ተሰማን ጨምሮ 10 ያህል ሲሆኑ በትላንትናው ዕለት ደግሞ ወህኒ ቤት እያሉ በጥይት የተደበደቡት ኮሎኔል ደምሰው አንተነህና ኮሎኔል አለሙ ጌትነትን ጨምሮ ሌሎች አባሪዎቻቸው ተፈተዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ እንዲሁም ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ጨምሮ ከ20 የሚበልጡ ጄኔራልና ከፍተኛ መኮንኖች በመንግስት ግልበጣ ተወንጅለው የታሰሩ ሲሆን፣በጄኔራሎቹ ላይ የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደም ማስታወስ ተችሏል።
በሐገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው ቀውስና የተከተለው ሕዝባዊ ግፊት ለፖለቲካ እስረኞቹ መለቀቅ በከፈተው ምቹ ሁኔታ ቀደም ሲል ዶክተር መረራ፣አቶ በቀለ ገርባና አቶ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም ከጋዜጠኞች እስክንድር ነጋና ውብሸት ታዬ መፈታታቸው ይታወቃል።በሳምንቱ መጀመሪያ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ የወልቃይት ማንነት ኮሚቴ አባላትም በተመሳሳይ ከወህኒ ወተዋል።
ሚያዚያ 16 ቀን 2001 ወደ ወህኒ የተጋዙት ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞና ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ጨምሮ ከ20 የሚበልጡት ጄኔራልና ከፍተኛ መኮንኖች ከግንቦት 7 ጋር በመቀናጀት መንግስት ለመገልበጥ ተንቀሳቅሰዋል በሚል መታሰራቸው ይታወሳል።
ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን በምርጫ 1997 ማግስት ለሕገ መንግስቱ ታማኝ አልሆኑም በሚል ማዕረጋቸውን ተገፈው ከሰራዊቱ ከተባረሩ ሶስት ጄኔራሎች አንዱ ናቸው።ከርሳቸው ጋር ማዕረጋቸውን ተገፈው ከሰራዊቱ የተባረሩት ሜጀር ጄኔራል አለምሸት ደግፌና ብ/ጄኔራል ኩመራ አስፋው ነበሩ።
የሕዝብ ድምጽ ይከበር በማለት የጠየቁና ሰራዊቱ ከፖለቲካ ገለልተኛ እንዲሆን በመንቀሳቀሳቸው ከሶስቱ ጄኔራሎች በተጨማሪ በርካታ ከፍተኛና መስመራዊ መኮንኖች ከሰራዊቱ ተባረዋል።
የፖለቲካ እስረኞችንና የሕሊና እስረኞችን የመልቀቁ ሒደት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ባልደረቦች እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣እንዲሁም ዶክተር ፍቅሩ ማሩ እና ዮናታን ተስፋዬ ዛሬም በወህኒ ቤት ይገኛሉ።