የሕወሃት ጨዋታ አበቃለት ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 15/2010)

“የሕወሃት ጨዋታ አበቃለት”ሲሉ የአሜሪካው ኮንግረስማን ዳና ሮራ ባከር ገለጹ።

የካሊፎርኒያው የሕዝብ ተወካይ ዳና ሮራ ባከር በቲውተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት አገዛዙ በመጨረሻ የሞት አፋፍ ላይ ያለና ያበቃለት ስርአት ነው።

ኮንግረስ ማኑ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ምክርቤት በተካሄዱ ውይይቶች ሕወሃት ኢትዮጵያን የማይወክልና በሀገሪቱ ለተፈጸሙ ግድያዎች እንዲሁም የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ተጠያቂ ነው ማለታቸውም ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ከሕዝቡ በደረሰበት ተቃውሞና ግፊት እየተዳከመና እየተፍረከረከ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።በሕወሃት/ኢሕአዴግ የሚመራው አገዛዝ የሕዝቡን ቁጣ ለማብረድ እየወሰደ ባለው የሃይል ርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለው ለእስርና ለመፈናቀል የተዳረጉት ደግሞ ለቁጥር አታካች መሆናቸው ነው የሚታወቀው።ይህም ሆኖ ግን የሕዝቡ አመጽ ባለመብረዱ የአገዛዙ ጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን መልቀቂያ እስከ ማቅረብም ደርሰዋል።በስርአቱ ውስጥ ጥገናዊ ለውጥ ለማምጣትም ሕወሃት በጥልቅ ተሃድሶ ስም ደፋ ቀና እያለ መሆኑ ይነገራል።ይህ በዚህ እንዳለም የአለምአቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ ለማግኘት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ አማካኝነት ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ የአሜሪካው ኮንግረስ ማን ዴን ሮራ ባከር ሕወሃት አበቃለት ሲሉ በቲውተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።ኮንግረስ ማኑ በአሜሪካ ምክር ቤት በተካሄዱ ስብሰባዎች ሕወሃት ኢትዮጵያን የማይወክልና በሃገሪቱ ላሉ ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ተጠያቂ ነው ማለታቸው አይዘነጋም።የአሜሪካ ኮንግረስ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ሁሉን አቀፍ አስተዳደር በሃገሪቱ እንዲኖር እና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስችል ኤች አር 128 የተባለ ረቂቅ ከማጽደቁ በፊትም በሂደት ላይ ይገኛል።ረቂቅ ሕጉን ለኮንግረስ አስቀርቦ ለማጸደቅም የኢትዮጵያው አገዛዝ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ የካቲት 28/2018 የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ወደ ሃገሪቱ እንዲያስገባ ጠይቋል።አገዛዙ ይህን ካልተቀበለ ኤች አር 128 በኮንግረሱ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።በተያያዝ ዜናም የጀርመን፣የሲውዲን እና የካናዳ ባለስልጣናት እንዲሁም የአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣቱን ተከትሎ የሃገሪቱ ሁኔታ እያሳሰባቸው መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።