በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የስራ ማቆም አድማ ተጀመረ
(ኢሳት ዜና የካቲት 12 ቀን 2010ዓ/ም) በጎንደር፣ በደብረታቦርና በባህርዳር ከተሞች ሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የስራ ማቆም አድማ ተጀምሯል። በጎንደር በመካሄድ ላይ ባለው አድማ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። የንግድ ድርጅቶችም እንዲሁ ተዘግተዋል። ወጣቶች በተለያዩ አደባባዮች ተሰባስበው በመታዬት የንግድ ድርጅቶችን ለማስከፈት የሚያስገድዱትን ባለስልጣናት ሲያስጠነቅቁ ታይተዋል። በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች የስራ ማቆም አድማው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኗል።
በባህርዳር በዋናው ገበያ አድማው ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ የጀመረ ሲሆን፣ የአገዛዙ ወታደሮችና የንግድ ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች በየንግድ ቤቶች በመዟዟር፣ ነጋዴዎችን በስልክ በመጥራትና በማስፈራራት የንግድ ድርጅቶች እንዲከፈቱ ሲያስገድዱ ታይተዋል። ማስጠንቀቂያውን የፈሩ ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን አረፋፍደው ሲከፍቱ፣ የንግድ ድርጅቶችን ለመክፈት ፈቃደና ያልሆኑት ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻቸው ታሽጎባቸዋል። በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር የፈሰሰ ሲሆን፣ በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና ለማሳረፍ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በወጣ ማግስት የተደረገው አድማ፣ አገዛዙ የህዝብን የለውጥ ጥያቄ በአዋጅ መመለስ እንደማይችል ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። በክልሉ ማንኛውም አይነት የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ በመሆኑ፣ መረጃዎችን ከወረዳ ወረዳ ለማሰራጨት አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገሩት በአድማው የሚሳተፉት ወጣቶች፣ ያ ሆኖ ያለውን ቀዳዳ ተጠቅሞ አድማ ለማድረግ መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
የአድማው ዋና ግብ የታሰሩት የህሊና እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱ ለመጠየቅና እስካሁን ህዝብ እየጠየቀ ያለው የዲሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ጫና ለመፍጠር ነው።
የአማራ ክልል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ከሁለት ቀናት በፊት በክልሉ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን፣ ሁሉም ነገር በመልካም ሁኔታ እየተጓዘ እንደሆነ ተናግረው ነበር። ባለስልጣኑ በተናገሩ ማግስት የስራ ማቆም አድማ መጀመሩ፣ የክልሉ ባለስልጣናት አሁንም ገና የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄ እንዳልገባቸው የሚያሳይ ነው የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
አድማው የታሰሩ የወልቃይት/ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች አስተባባሪዎች የሆኑት እነ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ፣ በመፍንቅለ መንግስት ሙከራ ተከሰው በእስር ያሳለፉት እነ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ፣ አሳምነው ጽጌ፣ ወ/ሮ እማዋይሽና ሌሎችም እስረኞች በተፈቱበት ማግስት የተደረገ ነው።