ከሰሜን ወሎ የታፈሱት ወጣቶች በስልጠና ወቅት ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር ታወቀ

ከሰሜን ወሎ የታፈሱት ወጣቶች በስልጠና ወቅት ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር ታወቀ
(ኢሳት ዜና የካቲት 12 ቀን 2010ዓ/ም) ከጥር 21 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ ከወልድያ፣መርሳና ሮቢት የተሰባሰቡ ዜጎች ጃሪ በሚባል የስሪንቃ እርሻ ምርምር የንብ ማንባት ምርምር የሚያደርግበት ጫካ ውስጥ መጣላቸውን የሚገልጹት ከእስር የተፈቱት ወጣቶች፣ ቦታው ፈፅም ለማረሚያ ቤት ያልተዘጋጀ መፀዳጃ ቤት የሌለው፣ውሀ ፣የህክምና ቦታ የሌለው ነበር ይላሉ። እስረኞቹ ሁኔታዎች ካልተሻሻሉ ምግብ አንበላም የሚል አድማ በመጀመራቸው ጊዜያዊ መፀዳጃ ቤት እና የውሃ አገልግሎት እንደተጀመረላቸው፣ ጥር 24 ቀን 2010 ዓም ደግሞ ወደ ስልጠና እንደገቡ ገልጸዋል። የስልጠና አጀንዳዎች የአማራ ክልል እና የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ልማት እና ጥፋት፣ ልማታዊ መንግስትና ኒዮ ሊብራሊዝም፣ ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና እና የቀለም አብዮት የሚሉ እንደነበሩ ሰልጣኖች ተናግረዋል።
እስረኞች “ የህዝብ ጥያቄ መልሱ፣ አለበለዚያ ምንም ዓይነት ምድራዊ ምክንያት ይህን የህዝባዊ ዓመፅ ሊያስቆም አይችልም” የሚሉ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። እስረኞች ወያኔ ለኢትዮጵያ መዋረድ ተጠያቂው ወያኔ ነው ያሉ ሲሆን፣ አሰልጣኖች “ኒዮ ሉብራሊዝሞች ይህን የህዝብ ብሶት ተጠቅመው በግንቦት ሰባት እና በግብፅ አማካይነት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለማድረግ ነው” በማለት ትንተና ሲሰጡ አጥብቀው ተቃውመዋል። “ትግሉ የህዝብ ነው። ትግሉን የሚመራው ህዝብ ነው” በማለት ጠንካራ ክርክር በማድረጋቸው አሰልጣኞች የእስረኞችን ሀሳብ ለመቀበል ተገደዋል ብለዋል።
አስልጣኞች የክልሉ መስተዳድር አማካሪ አቶ ግዛት አብዩ፣ የአመራር ማስልጠኛ ተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደሴ እና ሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣኖች ነበሩ።