(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 12/2010)
በአሜሪካ የአፍሪካውያን የመጀመሪያው ባንክ በኢትዮጵያውያን ሊቋቋም ነው።
“ማራቶን” የሚል ስያሜ የተሰጠውና ኑሯቸውን በውጭ ሀገር ባደረጉ ኢትዮጵያውያን የተመሰረተው ይህ ባንክ አስፈላጊዎቹን መመዘኛዎች አሟልቶ ለሚመለከተው አካል ማመልከቻውን ማስገባቱን ይፋ አድርጓል።
ማራቶን ኢንተርናሽናል ባንክ በሚል ስያሜ የተቋቋመው ይህ የኢትዮጵያውያን ባንክ በጥቂት ወራት ግዜ ውስጥ በዋሽንግተን ዲሲ የመጀመሪያውን የባንኩን ቅርንጫፍ እንደሚከፍት የባንኩ ህዝብ ግንኙነት ለኢሳት ከላከው መግለጫ መረዳት ተችሏል።
በባንክ ሙያ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሚስተር ግሬግ ጋሬት የተባሉ ባለሙያ የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ እንደሚሆኑም ተመልክቷል።
ኑሯቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉ በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን እምቅ አቅም ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና በስራ ፈጠራም ጭምር ለማገዝ ባንኩ መቋቋሙ ተገልጿል።
በአሜሪካ ውስጥ የተቋቋመ የመጀመሪያው የአፍሪካውያን ባንክ እንደሚሆንም ተመልክቷል።
በቅርቡ የመጀመሪያውን የባንክ ቅርንጫፍ በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚከፍት የተገለጸው ማራቶን ባንክ በመላው አሜሪካ ቅርንጫፍ ባንኮች እንደሚኖሩትም ከጋዜጣዊ መግለጫው መረዳት ተችሏል።
ፒው የተባለው የአሜሪካውያን የጥናት ቡድን ባወጣው መረጃ መሰረት በአሜሪካ ከሚኖሩ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን አፍሪካውያን ውስጥ በብዛት ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት ናይጄሪያውያን ሲሆኑ ቁጥራቸውም 327ሺ እንደሆነ ተመልክቷል።
በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ቁጥራቸውም 222ሺ ነው።
ግብጻውያን 192ሺ በመሆን ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ይህ ቁጥር አሜሪካ የተወለዱትን አይጨምርም።