(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 8/2010)
የክራርና የዋሽንት ሊቅ በሚል የሚታወቁትና የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩት አቶ መላኩ ገላው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ሕይወታቸው ያለፈው የአቶ መላኩ ገላው አስከሬን ዛሬ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተልኳል።
ከአባታቸው ከአቶ ገላው ወልደተክሌና ከእናታቸው እማሆይ ትኩነሽ ተሰማ መጋቢት 12/1931 የተወለዱት አቶ መላኩ ገላው ከ1956 ጀምሮ በኢትዮጵያ የባህላዊ መሳሪያዎች በተለይም በክራርና ዋሽንት ተጫዋችነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
በቀድሞው በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ስር ባለው የኢትዮጵያ ኦርኬስትራ የባህል ቡድን ውስጥ የኪነጥበብ ሙያቸውን የጀመሩት አቶ መላኩ ገላው ከ1959 ጀምሮ ለ27 አመታት በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል።
የዛሬ ሃያ አመት ከነቤተሰባቸው ወደ አሜሪካ የተጓዙት አቶ መላኩ ገላው በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የክራር ትምህርት ቤት በመክፈት ሙያቸውን በባዕድ ሀገርም ለመቀጠል ያደረጉት ሙከራም በሕይወት ታሪካቸው ላይ ተመልክቷል።
አቶ መላኩ ገላው ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት በ79 አመታቸው ሕይወታቸው አልፏል።
የቀብራቸውም ስነስርአት በትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የሚፈጸም ሲሆን አስከሬናቸውም ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ መጓዙ ታዉቋል።
አቶ መላኩ ገላው ባለትዳርና የ7 ልጆች አባት ነበሩ።