(ኢሳት ዜና የካቲት 6ቀን 2010ዓ/ም) አቶ በቀለ ገርባና 6 ጓደኞቻቸው ከእስር ተለቀቁ
ባለፉት 2 ቀናት በኦሮምያ የተለያዩ አካባቢዎች የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ የኦፌኮ ም/ል ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ገርባ ፣ ጉርሜሳ አያና፣ አዲሱ ቡላላ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ ጌቱ ጋሩማ፣ ተስፋዬ ሊበን እና በየነ ሩዳ ከእስር ተፈተዋል። ሰሞኑን ችሎት በመድፈር የአንድ አመት እስር የተፈረደባቸው እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ ፍርዳቸውን ሳይጨርሱ መፈታታቸው ውሳኔውን ላስተላለፉት ዳኞች ትልቅ ውርደት፣ ለመብታቸው በመታገል ላይ ላሉት ቄሮ እየተባሉ ለሚጠሩት ወጣቶች ደግሞ ታላቅ ድል ተደርጎ ተቆጥሯል።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ይፈታሉ የተባሉት እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አንዱለአም አራጌና ሌሎችም እስረኞች የይቅርታ ፎርም እንዲሞሉ ተጠይቀው አሻፈረን በማለታቸው አሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በመፍንቅለ መንግስት ሙከራ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ከመፈታታቸው በፊት የሚሰጠውን ተሃድሶ በመውሰድ ላይ እያሉ፣ አብረዋቸው የተከሰሱት እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ካልተፈቱ አልፈታም በማለታቸው ተሃድሶውን አቋርጠው በመውጣት ወደ ቃሊቲ እስር ቤት መመለሳቸው ታውቋል። ወ/ሮ እማዋይሽ በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል። አሁን የወሰዱት እርምጃ ብዙዎች አድናቆታቸውን በፌስቡክ እየገለጹ ነው፡