ጃኮብ ዙማ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ተጠየቁ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 6/2010)

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ፓርቲያቸው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ማሳሰቢያ ሰጠ።

ሁለተኛውን ዙር የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸውን ለማጠናቀቅ የአንድ አመት ግዜ የቀራቸውና በርካታ የሙስና ወንጀሎች የቀረቡባቸው ዙማ ፓርላማው የመተማመኛ ድምጽ ሳይነፍጋቸው በፈቃዳቸው ስልጣን እንዲለቁ የሚደረገው ግፊት ተጠናክሯል።

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ /ኤ ኤን ሲ/ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጃኮብ ዙማን በተመለከተ 13 ሰአታት የፈጀ ስብሰባ ካካሄደ በኋላ በስልጣን መልቀቂያው ላይ ቀነ ገደብ እንዳስቀመጠ ቢገለጽምየፓርቲው ባለስልጣናት የተቀመጠ ቀነ ገደብ አለመኖሩን አስታውቀዋል።

ሆኖም ምላሻቸው እምቢታ ከሆነ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ውይይት እንደሚያካሂድ የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ኤሲ ማጋሼል ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ዋና ጸሓፊ ለመገናኛ ብዙሃን ጨምረው እንደገለጹት በሃገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትና የፓርቲውን የመሪነት ስፍራ የያዙት ሲሪል ራምፎሳ፣ ጃኮብ ዙማን ተክተው እስከ 2019 የሃገሪቱን የመሪነት ስፍራ እንዲረከቡ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ እንደሚፈልግ አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በይፋ ስልጣን እንዲለቁ የጠየቃቸው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ነገ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ በመጠበቅ ላይ ነው።

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበርነቱን ባለፈው ታህሳስ ለሲሪል ራምፎሳ ያስረከቡት ጃኮብ ዙማ የሃገሪቱን የመሪነት ስፍራ በተመሳሳይ እንዲያስረክቡ ግፊቱ የተጠናከረው ከዚያህ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነም ታውቋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1958 የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስን የተቀላቀሉትና ለፓርቲያቸው ታማኝና ጠንካራ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ጃኮብ ዙማ የደቡብ አፍሪካን የነጮች መንግስት በመገልበጥ ሙከራ ተወንጅለው አስር አመታት ተፈርዶባቸው በሮቢን አይላንድ እስር ቤት አሳልፈዋል።

ከእስር ከተፈቱ በኋላ በስደት በትግሉ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውም ታውቋል።

ወደ ስልጣን ለመውጣት ጉዞ ከጀመሩበትና ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ የሴት መድፈርን ጨምሮ በርካታ የሙስና ወንጀሎች ሲቀርብባቸው ቆይቷል።

የስልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ አንድ አመት በቀረው በዚህ ሰአት የተጠናከረው እሳቸውን ከስልጣን የማስወገድ ዘመቻ ምክትላቸውን ሲሪል ራምፎሳን በመተካት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የ75 አመቱን ጃኮብ ዙማን የሚተኩት የ65 አመቱ ራምፎሳ በደቡብ አፍሪካ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1990 ማንዴላ ከወህኒ ከወጡ በኋላ በ1991 የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ጸሃፊ ሆነው አገልግለዋል።

በደቡብ አፍሪካ አዲስ የሽግግር ስርአት ለመመስረት በተደረገው ድርድር የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስን የወከሉ ቁልፍ ተደራዳሪ እንደነበሩም መረዳት ተችሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1994 ኔንሰን ማንዴላ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ በምክትልነት ይመረጣልይ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ሆኖም ታቦ ምቤኪ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው ማንዴላን የመተካት እድላቸው ያኔ ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ዛሬ ላይ ግን የደቡብ አፍሪካን የመሪነት መንበር ለመያዝ ከጫፍ ደርሰዋል።