ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን በመገደብ ሁለተኛ ሆነች

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2010)

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን በመገደብ ከቻይና ቀጥሎ በአለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች መባሉን የሀገሪቱ አገዛዝ አስተባበለ።

በሕወሃት የሚመራው አገዛዝ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል በሰጠው መግለጫ ኢንተርኔት በኢትዮጵያ ተዘግቶ አያውቅም ሲል አስተባብሏል።

ፍሪደም ሃውስ የተባለው አለም አቀፍ ድርጅት ሰሞኑን ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን በማፈን ከአለም ከቻይና ቀጥሎ 2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች የሚል ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።

በፍሪደም ሃውስ ሪፖርት መሰረት ቻይና፣ ኢትዮጵያና ሶሪያ ኢንተርኔትን በማፈን ቀዳሚ ሀገራት ሆነዋል።

የኢንተርኔት ነጻነት አስተማማኝ የሆነባቸው ሀገራት አይስላንድና ኢስቶኒያ ናቸው ሲል ሪፖርቱ በቀዳሚነት አስቀምጧቸዋል።

የሀገራት የኢንተርኔትና ስልክ መገናኛ መንገዶች አጠቃቀምን ያመለከተው ይህው የፍሪደም ሀውስ ሪፖርት ኢትዮጵያ በተለይ የመብት ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ኢንተርኔትን ሙሉ በሙሉ ትዘጋለች ሲል ተናግሯል።–በተለይ ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች።

ሪፖርቱ ማህበራዊ ድረ ገጾችና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ድረ ገጾች ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ እንደሚዘጉ አረጋግጧል።

ፍሪደም ሃውስ እንደገለጸው የኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ አገልግሎት በጣም ውድ ከሆነባቸው ሃገራት ኢትዮጵያ ዋነኛዋ ናት።

የሃገሪቱ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ደካማ መሆኑንና በመንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ነው ሪፖርቱ የገለጸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ኢንተርኔትን አፍኜ አላውቅም ብሏል።

ፌስ ቡክና ሌሎች ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተዘግተው የሚያውቁት በብሔራዊ የተማሪዎች ፈተና ወቅት ብቻ ነው በማለት የአገዛዙ ሪፖርት አመልክቷል።

ኢትዮ ቴሌኮም የፍሪደም ሃውስን ሪፖርት ተዓማኒነት የሌለው ሲል ኮንኖታል።

እንደ ኢትዮ ቴሌኮም አገላለጽ ፍሪደም ሃውስ የቴሌኮም ይዞታን በብቃት የመገምገም ስልጣን የለውም።

ይህን ማድረግ የሚችለው አለምአቀፉ የቴሌኮም ሕብረትና አይ ሲቲ አፍሪካ ናቸው ባይ ነው ኢትዮ ቴሌኮም ።

በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ይህን ይበል እንጂ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም።