(ኢሳት ዲሲ–ጥር 15/2010)
በወልዲያ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ የሃይማኖት አባቶች አወገዙት።
በውጭ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገር ቤት የሚገኘው ቤተክህነት በጉዳዩ ላይ ዝምታን መመረጡ እጅግ እንዳሳዘናት በመግለጽ መግለጫ አውጥታለች።
የፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን ኢማም ሼህ ካሊድ ኡመር የከፋ እልቂት ከመከሰቱ በፊት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሰከን እንዲል ጥሪ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ መስራች ወንጌላዊ ዳንዔል ጣሰው ግድያውን የፈጸሙ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን ብለዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የወልዲያው ጭፍጭፋ የህወሀት አገዛዝ በራሱ እንደማይለወጥ ማረጋገጫ ነው ሲል ድርጊቱን በማወገዝ መግለጫ አውጥቷል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች በጋራ የወልዲያውን እልቂት አውግዘዋል።
በውጭ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መቆሚያ ያጣ የዋይታ ጉዞ በሚል ርዕስ ባወጣችው መግለጫ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ በስልጣን ላይ ባለው አገዛዝ እየተፈጸመ ያለው ግድያ፣ በወልዲያም በስርዓተ አምልኮ ላይ በነበሩ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው እልቂት ቤተክርስቲያኒቱን እንዳሳዘናት አስታውቃለች።
የሲኖዶሱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቡነ ጴጥሮስ እንደሚሉት በዚህን ወቅት በሀገር ቤት ያለው ቤተክህነት ዝምታን መምረጡ ጉዳዩን አሳዝኝ አድርጎታል።
የየቀኑ የሀዘን እንጉርጎሮ ቀጥሏል ያሉት አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያውያን በሰላም መብታቸውን በመጠየቅ ትግላቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን ኢማም ሼህ ካሊድ ኡመር በንጹሃን ላይ የሚወሰደው ርምጃ በወልዲያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሆነ ገልጸው የህወሀት አገዛዝ ሰከን ማለት አለበት ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሼክ ካሊድ እንደሚሉት የህወሃት አገዛዝ እንዲህ ዓይነት የግድያ ርምጃ የሚወስደው ህዝብን በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻሉ ነው።
ህዝባችን የብሄርና የሃይማኖት ልዩነቱ ወደ ግጭት እንዳይመራው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ሼክ ካሊድ ጥሪ አድርገዋል።
የተነሺ ኢትዮጵያ ተልዕኮ መስራች ወንጌላዊ ዳንዔል ጣሰው በበኩላቸው ግድያው እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፡ ይህን በንጹሃን ላይ የግፍ ተግባር የፈጸሙ ወገኖች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን ብለዋል።
የወልዲያ ወጣቶች አስቸኳይ መፍትሔ ሲጠይቁ ለነገ ሳይሆን ለዛሬ እንዲሆን ነው ማለታቸውን ጠቅሰው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ በወልዲያ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ፣ ምህዳሩን አሰፋለሁ ሲል የሰነበተው የህወሃት አገዛዝ ወደተካነበት የጅምላ ግድያው ተመልሶ ገብቷል ሲል ያወገዘው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ አገዛዙ በራሱ መለወጥ እንደማይችል ያረጋገጠበት የጭካኔ ርምጃውን በወልዲያ ፈጽሟል ብሏል።
ይህ ድርጊት ለነጻነትና ዲሞክራሲ መስፈን ለሚታገሉ ሃይሎች ይበልጥ የሚያነሳሳ እንጂ በሀዘን እንድንሰበር የሚያደርግ አይደለም ብሏል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ።
ይህ ቅጥ ያጣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ በደልና አፈና አብቅቶ ሀገራችን በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ወደ ዘላቂ ሰላም እንድታመራ ንቅናቄው ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።