(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2010)
በኢትዮጵያ የሚከበረውን አመታዊ የጥምቀት በአልና የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች መኖራቸውን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
በመንግስታዊና በፓርቲ መገናኛ ብዙሃን የተለቀቀው የፌደራል ፖሊስ መግለጫ አደጋውን ለመጣል እየተንቀሳቀሱ ያሉት ሃይሎች እነማን እንደሆኑ ግን ግልጽ አላደረገም።
የፖለቲካ ምሁራን ይህን የፌደራል ፖሊስ መግለጫ ሕዝብን የማሸበር ርምጃ ሲሉ ተችተውታል።
አንዳንዶቹ ስልጣን ላይ ያለውን ቡድን የቀደመ ተግባር እየጠቀሱ ራሱ አደጋ ለመጣል አስቦ ይሆናል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በመንግስታዊው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንዲሁም የሕወሃት ንብረት በሆነው ሬዲዮ ፋና የተሰራጨው የፌደራል ፖሊስ መግለጫ በአሉ በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ማጠናቀቁንም ይገልጻል።
ሆኖም የጥምቀት በአልና የፊታችን ሰኞ የሚጀመረውን የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ስለመኖራቸው መረጃ ደርሶኛል ሲል አስታውቋል።
ሁከት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱት ሃይሎች ከአዲስ አበባ ባሻገር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መሰማራታቸውንም መግለጫው ገልጿል።
የህብረተሰቡንም ትብብር ጠይቋል።
ሁከት ለመፍጠር ተዘጋጅተዋል የተባሉት ሃይሎችን ማንነትና ሁከት የሚፈጥሩትን ሃይሎች ኢላማ ያላብራራው መግለጫ ከአዲስ አበባ ውጪ ሁከት ፈጣሪዎቹ በየትኞቹ አካባቢዎች ላይ እንዳነጣጠሩም በዝርዝር አላስቀመጠም።
ይህን መግለጫ ያወጣው የመንግስት የጸጥታ መዋቅር የፌደራል መደበኛ የጸጥታ ኮማንድ ፖስት ነው በማለት ራሱን አስቀምጧል።
ነገር ግን ይህ አደረጃጀት ከዚህ ቀደም ተሰምቶ አይታወቅም።
የፖለቲካው ዘርፍ ባለሙያዎች ሕዝብ አመታዊውን ታላቅ ሃይማኖታዊ በአል ከተራና ጥምቀትን ለማክበር በተዘጋጀበት ህዝብ የሚያሸብር መግለጫ እንዴት ያወጣል በማለት ጠይቀዋል።
ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ሲሉም ኮንነዋል።
በሌላም በኩል ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ከዚህ ቀደም የፈጸማቸውን ድርጊቶች እየጠቀሱ ራሱ ሁከት ሊፈጥር አስቦ ይሆናል በማለት ስጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖችም አሉ።
መግለጫው መውጣቱን ተከትሎም በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ከፍተኛ ትችቶች በመሰንዘር ላይ ናቸው።
በሕወሃት መሪዎች የሚታዘዘው የሀገሪቱ የደህንነት መዋቅር ሰላማዊ ሰዎችን ለማሰር እንዲሁም ሕዝብን ስጋት ውስጥ ለመጣል ራሱ ፍዳታዎችን ሲያቀነባብር መቆየቱ ሲገለጽ ቆይቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 6/2006 አዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በወቅቱ የሃገሪት ጉዳይ ፈጻሚ ከነበሩት አምባሳደር ቪኪ ሃድልስተን ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተላከው የኬብል መልዕክት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 16/2006 አዲስ አበባ የፈነዳውንና በኦነግ የተሳበበውን ፍንዳታ የሀገሪቱ ደህንነቶች እንደፈጸሙት በዊክሊክስ መጋለጡ ይታወሳል።