የኢኮኖሚ ቀውሱ የህወሃትን አገዛዝ ለተፋጠነ ውድቀት ሊዳርገው ይችላል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010)

በኢትዮጵያ የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ የህወሃትን አገዛዝ ለተፋጠነ ውድቀት ሊዳርገው እንደሚችል ተገለጸ።

ኢሳት ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት የፖለቲካ አለመረጋጋት እየናጠው ያለው አገዛዝ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መግባቱ ውድቀቱን እያፋጠነው ነው።

ሀገሪቱ የገጠማት የኢኮኖሚ አደጋ አሁን በስልጣን ላይ ባለው አገዛዝ አቅም የሚፈታ ባለመሆኑ ህዝባዊ አመጾች ሚነሱበት እድል ሰፊ ነው ሲሉ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

የአገዛዙ ደጋፊ መገናኛ ብዙሃንም የኢኮኖሚ ቀውሱን በመጥቀስ ከፍተኛ አደጋ እየመጣ ነው ሲሉ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ነው የሚለው ድምጽ እየጎላ የመጣው ከብዙ አቅጣጫ ነው።

በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ኢኮኖሚውን አንኮታክቶታል የሚለው አስተያየት ተጠናክሮ መሰማቱን ቀጥሏል።

የውጭ ምንዛሪ ክምችት በአስደንጋጭ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሀገሪቱ ያላት የውጭ የምንዛሪ ክምችት ከ1ቢለየን ዶላር በታች 700ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ ቀጥ ብሎ ከሚቆምበት ምዕራፍ ተጠግቷል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ለመድሃኒት መግዣ በሚል የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ከአንድ ወር በላይ የማያዛልቅ መሆኑ አደጋውን የበለጠ ያሰፋዋል ብለዋል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቀድሞውኑም የተበላሸው የኢኮኖሚ ገጽታ በፖለቲካው ትርምስ ምክንያት ቀና ከማይልበት ደረጃ ላይ ይገኛል።

በሀገሪቱ በየአቅጣጫው የተነሳው የህዝብ አመጽ በዋናነት የኢኮኖሚ ጥያቄ ማጠንጠኛ መሆኑን የሚጠቅሱት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የአገዛዙ ውድቀት ከሚጠበቀው በላይ በፍጥነት ሊሆን እንደሚችል ምልክቶቹ በሚገባ እየታዩ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እንዳሉት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት ወደቀውስ እየገባች ነው። ኢኮኖሚው ወድቋል። አገዛዙ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ተስኖታል።

አንድ ሊፈራርስ የተቃረበ ስርዓት የሚታዩብት ምልክቶች አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጠው በመታየት ላይ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ለአገዛዙ ቅርበት ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ ዘገባ ያወጣው ህወሃት የገጠመው የኢኮኖሚ ቀውስ መደበቅ ከማይቻልበት ጊዜ ላይ በመድረሱ ነው ሲሉ ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

እንደሪፖርተር ዘገባ ከሆነ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንደበረዶ እየቀለጠ ነው። የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ መቀነስ ታይቶበታል።

የንግድ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል። የግብይት ስርዓት ትርምስ ውስጥ ገብቷል። የቱሪዝም ፍሰቱ አደጋ ውስጥ ወድቋል።

የዋጋ ግሽበቱ ወደሁለት አሃዝ ሲገባ የብር የመግዛት አቅም መቀነሱ ይበልጥ ኢኮኖሚውን አሽመድምዶታል።

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሀገሪቱ እጅና እግሯ ተሳስሯል ሲል ቀውሱን በዝርዝር የገለጸው ሪፖርተር ጋዜጣ ይህ ሁኔታ በፍጥነት ካልተቀየረ አደጋው ከባድ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

የሪፖርተር ስጋት የአገዛዙ መውደቅ መሆኑ በግልጽ ያሳያሉ የሚሉ ታዛቢዎች ሊደበቅ የማይችለውን ቀውስ በአገዛዙ መገናኛ ብዙሃን ማስተንፈስ እንደአንድ ስልት ሊወሰድ ይችላል ሲሉም ግምታቸውን ገልጸዋል።

በአሜሪካ ቨርጂኒያ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ዘላለም ተክሉ እንደሚሉት የፖለቲካውና የኢኮኖሚው ቀውሶች በአንድ ጊዜ ጎን ለጎን መከሰታቸው የህወሀትን አገዛዝ ውድቀት አይቀሬ አድርጎታል።