የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ታሰሩ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010)

በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች መታሰራቸው ተገለጸ።

ትላንት በአዲስ አበባ ስታዲየም የተደረገውን የመቀሌ ከነማና የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ግጥሚያን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ከባድ ድብደባ እንደደረሰባቸው ታውቋል።

ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ደጋፊዎችም ታፍሰው መታሰራቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።

በተለያዩ የአዲስ አበባ እስር ቤቶች የሚገኙት ደጋፊዎች ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎም እየተጠበቀ ነው።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወደ አዲስ አበባ የተዛወረው በጎንደር ወይም በመቀሌ ለማካሄድ የጸጥታ ችግር በመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።

ከጎንደር በበርካታ አውቶቡሶች አዲስ አበባ የገቡት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የአጼ ቴድሮስን ልደት ምክንያት በማድረግ ቲሸርት አሳትመው በመልበስ ስታዲየሙን አድምቀውት እንደነበር ከተሰራጩት ቪዲዮዎች መረዳት ተችሏል።

በፖለቲካ መልዕክቶች የተሞላው የ90ደቂቃ ጨዋታ ያለምንም ግብ ዜሮ ለዜሮ የተጠናቀቀ ሲሆን በስታዲየም ውስጥ የህወሃትን አገዛዝ የሚያወግዙ መዝሙሮችና መፈክሮች ይሰሙ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

በተለይም የወልቃይት ጉዳይ በጨዋታው ጊዜ በደጋፊዎች ተነስቶ የታፈነ ድምጽ ሲስተጋባ ነበር ተብሏል።

ጨዋታው ካበቃም በኋላ ከስታዲየም ውጭ የነበረው ተቃውሞ ከፖሊስ ጋር ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል።

ስታዲየም አካባቢ በፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ‘’ወያኔ ሌባ’’ በሚል ተቃውሞ የተሰማ ሲሆን የአዲስ አበባ ነዋሪም ተቀላቅሎ ስሜቱን መግለጹን በተሰራጨው ቪዲዮ ላይ መመልከት ተችሏል።

የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን ካሰሙ በኋላ ከፖሊስ ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።

ፖሊስ በወሰደው ርምጃ በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን መረጃዎች ያመልክታሉ።

አምባሳደር ቲያትር ቤት አካባቢ ከ100 በላይ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ታፍሰው መወሰዳቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

አምባሳደር አካባቢ ሌላ በስታዲየምና ሜክሲኮ የአጼ ቴዎድሮስ ምስል ያለበትን ቲሸርት የለበሰ እየተለቀመ ወደ ተለያዩ እስር ቤቶች መወሰዱንም ለማወቅ ተችሏል።

የተለያዩ የመረጃ ምንጮች እንዳረጋገጡት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችን ጨምሮ የአጼ ቴዎድሮስ ምስል ያለበትን ቲሸርት የለበሱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአራት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢዎች ታስረው እንደሚገኙ ተገልጿል።

እነዚህ በፒያሳ ጣይቱ ፓሊስ ጣቢያ፣ በወረዳ 9 ፣ በራስ ደስታና በጃን ሜዳ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የሚገኙ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በቤተሰብ እንዳይጠየቁ መከልከላቸውም ታውቋል።

ለጊዜው ቁጥራቸውን በውል ማወቅ ያልተቻለውና ከ100 እስከ 150 ይደርሳሉ በሚል የሚገመቱትና በእስር ላይ የሚገኙት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የታወቀ ነገር የለም።

ፖሊስ ለምን እንዳሰራቸውም በይፋ አልገለጸም።

ባለፈው ሳምንትም በተመሳሳይ የወልዲያ ከነማ ከትግራዩ ወልዋሎ ክለብ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም በነበራቸው ጨዋታ ላይ ከፖሊስ ጋር ግጭት መፈጠሩ የሚታወስ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስፖርታዊ መድረኮች የተቃውሞ ስሜት መግለጫ መሆናቸው እየተለመደ መምጣቱ በተለይ የትግራይ ክለቦች ከአዲስ አበባ ውጪ ለመጫወት እንዳልቻሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በአንጻሩ የአማራና የኦሮሚያ ክለቦች ሲገናኙ የሚደረገው አቀባበል እየተጠናከረ መጥቷል።

ችግሩ በትግራይ ብቻ እንዳልሆነ ለማሳየትም ባለፈው ሳምንት በባህርዳሩ አውስኮድና በወለጋው ነቀምት ክለቦች መሃል በባህር ዳር ሊደረግ የታቀደውን ውድድር በህወሀት አገዛዝ ጫና ምክንያት በአዲስ አበባ እንዲደረግ መወሰኑ የሚታወስ ነው።