አራት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተገደሉ 10 ቆሰሉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010)

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ታጣቂዎች አራት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን መግደላቸውንና 10 ማቁሰላቸው ተገለጸ።

ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በ14 የፖለቲካ እስረኞች ላይ የጥፋተኝነት ብይን ተሰቷል።

በችሎቱ እንደተገለጸውም የንቅናቄው ታጣቂዎች በ2007 በሁመራ በኩል በመግባት በሰነዘሩት ጥቃት የመንግስት ወታደሮች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉም ውሳኔ አሳልፏል።

በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከሰኔ 25 እስከ ሰኔ 28 2007 የተደረገው ውጊያ ነው ዛሬ በፍርድ ቤት ክስ ሆኖ የተነበበውና ብያኔ የተሰጠው።

ከክሱ መረዳት እንደተቻለው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ታጣቂዎች በቃፍታ ሁመራ በኩል ሰርገው በመግባት ከትግራይ ክልል ሚሊሺያ፣ ልዩ ሃይልና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ውጊያ ይገጥማሉ።

ለአራት ቀናት ውጊያ መደረጉን በወቅቱ በኢሳትና በሌሎች የዜና ምንጮች የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ መረጃውን ሀሰት በማለት የህወሀት አገዛዝ መገናኛ ብዙሃን ማጣጣላቸው የሚታወስ ነው።

ነገር ግን ውጊያ መደረጉንና በዚህም ውጊያ አራት የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ተገድለዋል ሲል በክስ መዝገቡ ላይ ተብራርቷል።

ሌሎች 10 የሰራዊቱ አባላትም በውጊያው እንደቆሰሉ ተጠቅሷል።

በአንድ መዝገብ የተከሰሱትና በስም የተዘረዘሩት የንቅናቄው ታጣቂዎች ገብሬ ንጉሴ፣ አገናኝ ካሱ፣ ስማቸው አምበሉ፣ ባባዬ አዛናው፣ አስቻለው ክፍሌ፣ ደሴ ክንዴ፣ ክብረት አያሌው፣ ብርሃን ዳርጌ፣ አወቀ መኮንን፣አበረ ፋንታሁን፣ሻንቆ ብርሃኑ፣ ጌትነት ዘሌ፣ ተሻገር መስፍን እና ሰጤ ጎባለ ናቸው።

በክስ መዝገቡ ላይ እንደተብራራው የንቅናቄው ታጣቂዎች በትግራይ ክልል ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ እንዲሁም በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኛቸው እንዲከላከሉ ሲል ብይን መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል።

ከተከሳሾቹ 9ኙ አንከላከልም በማለታቸው የመጨረሻ ብይን ሊሰጣቸው ለጥር 17 ቀጠሮ መሰጠቱ ተገልጿል።

እንከላከላለን ያሉት ቀሪዎቹ ተከሳሾች ምስክር እንዲያቀርቡ ለየካቲት 8 2010 መቀጠሩም ተመልክቷል።

አርበኞች ግንቦት ሰባት በተደጋጋሚ በመንግስት የተለያዩ የጸጥታና የመከላከያ ተቋማት ላይ ጥቃት እንደሚያደርስ ሲገልጽ ቢቆይም የህወሃት አገዛዝ ሲያስተባብልና ሲያጣጥል እንደነበረ የሚታወስ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የፍርድ ቤት ችሎቶች ላይ አርበኞች ግንቦት ሰባት አደረስኩ የሚላቸው ጥቃቶች ማረጋገጫ እየተሰጣቸው ነው።

ከአንድ ወር በፊት በህወሃት ንብረት በሆነው ሰላም ባስ ዋና ጋራዥ ጥቃት መሰንዘሩን በፍርድ ቤት በቀረበ ክስ መረጋገጡ ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሰሞኑን አደረስኩ ባለው ጥቃት ድል እንደቀናው አስታውቋል።

ንቅናቄው ለኢሳት በላከው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው በሰሜን ጎንደር ዞን በለሳ አርባያ ወረዳ ጣና ኢየሱስ በተባለ ስፍራ የንቅናቄው ታጣቂዎች በፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት የወረዳው የጸጥታ ምክትል ሃላፊ አቶ በላቸው ፍቃዴ ሲገደል ሌላ የመንግስት ታጣቂ ጉዳት ደርሶበታል።

ይህን ጥቃት በተመለከተ ከህወሀት አገዛዝ በኩል ማስተባበያም ማረጋገጫም አልተሰጠም።