(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 26/2010)
ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ፣መምህርና የፖለቲካ ጉዳዮች ጸሐፊ ኢብራሂም ሻፊ በስደት በሚኖርባት ኬኒያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
በሌላ በኩል አንጋፋው የህክምና ባለሙያ ፕሮፌሰር ዕደማርያም ጸጋ ተሻለ በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ኢብሮ በአጭሩ የሚጠራበት ስሙ ነው። መምህር ሆኖ አገልግሏል። የስፖርት ጋዜጠኝነቱ በሰፊው ይነሳለታል።
የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሚሰጣቸው ትንተናዎችም ይታወቃል። በሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግም አስተዋጽኦው የጎላ ነው።–ጋዜጠኛና መምህር ኢብራሂም ሻፊ።
ያስተማራቸው ተማሪዎቹ፣ የስፖርት ቤተሰቡ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተለው ሁሉ ዛሬ ጥሩ ዜና አልሰማም።
በህወሀት አገዛዝ አፈና ለስደት የተዳረገው ኢብራሂም ሻፊ ትላንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ጋዜጠኛ ኢብራሂም በ1997 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከተካሄደው ምርጫ በኋላ በጅምላ ታፍሰው በተለያዩ እስር ቤቶች ከተጋዙት መካከል አንዱ ነበር።
በሸዋሮቢት በእስር ላይ በነበረ ጊዜ በአገዛዙ ታጣቂዎች በደረሰበት ድብደባና ማሰቃየት የተነሳ ለህልፈት ለተዳረገበት በሽታ መንስዔ እንደሆነው የቅርብ ጓደኞቹ ይናገራሉ።
በስፖርት ጋዜጠኝነቱ ትልቅ ተቀባይነትን ያተረፈው ኢብራሂም በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የአገዛዙን ተግባራት በማጋለጥ በሳል የሆኑ ጽሁፎችን በተከታታይ በማውጣትም ብዙ አድናቂዎችንና ተከታዮችን አፍርቷል።
በተለይም አዲስ ጉዳይ የተሰኘው ሳምንታዊ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ በመሆን መስራቱ ከአገዛዙ ተደጋጋሚ ወከባ እንዲደርስበት አድርጓል።
አዲስ ጉዳይ በህወሀት አገዛዝ በደረሰበት ጫና ሲዘጋ ጋዜጠኛ ኢብራሂምም የመታሰር አደጋ ውስጥ መግባቱን የቅርብ ጓደኞቹ ይገልጻሉ።
በ2014 እንደ አውሮፖውያኑ አቆጣጠር ወደኬኒያ የተሰደደው ጋዜጠኛ በስደት ህይወቱም በተለይ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ በሸዋሮቢት በደረሰበት ድብደባ ምክንያት የገጠመው ጉዳት በስደት እያለ ወደጽኑ ህመም ተቅይሮ በመጨረሻም ለህልፈት አብቅቶታል።
የጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ የቀብር ስነስርዓት በሀገር ቤት እንደሚፈጸምም ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል አንጋፋው የህክምና ባለሙያ ፕሮፌሰር ዕደማርያም ጸጋ ተሻለ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
በአውሮፓ፣በሰሜን አሜሪካና በኢትዮጵያ በከፍተኛ የህክምና ተቋማት በማስተማርና በምርምር ስራዎች በርካታ ተግባራትን በማከናወን የሚታወቁት ፕሮፌሰር ዕደማርያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ፋኪሊቲ ለ23 ዓመታት ማገልገላቸውን ከህይወት ታሪካቸው ለመረዳት ተችሏል።
በካናዳ፣ በለንደንና በስዊዲን ተከታታይ የህክምና ትምህርታቸውን በመከታተል ለከፍተኛ ማዕረግ እንደበቁም የታሪክ ማህደራቸው ላይ ተጠቅሷል።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመጀመሪያውን የኢንዶስኮፒ አገልግሎትም በማቋቋም የሚታወቁ ናቸው።
በ1927 በጎንደር የተወለዱት ፕሮፌሰር ዕደማርያም ጸጋ ተሻለ በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ፕሮፌሰር ዕደማርያም ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነበሩ።