በኢራን እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ በኢራን ጠላቶች የተቆሰቆሰ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2010)

በኢራን እየተካሄደ ያለውን ጸረ መንግስት ተቃውሞ የሀገሪቱ መንፈሳዊ መሪ በኢራን ጠላቶች የተቆሰቆሰ ነው ሲሉ ወነጀሉ።

መንፈሳዊ መሪው አያቶላ አሊ ካሚኒ ባለፈው ሐሙስ ተቃውሞ ከተነሳ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ጠላቶች ያሏቸውን አካላት በግልጽ አልተናገሩም።

በኢራን እየተካሄደ ባለው ጸረ አገዛዝ ተቃውሞ ተጨማሪ ሕይወት መጥፋቱን መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።

መንፈሳዊ መሪው ኦፊሴላዊ በሆነው ድረገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት የተቃውሞው ጠንሳሾች የሀገሪቱ ጠላቶች ናቸው ብለዋል።

የኢራን ጠላቶች ያሏቸውን በግልጽ ባያስቀምጡም የፖለቲካ ተንታኞች እስራኤን፣ሳውዳረቢያንና አሜሪካን መወንጀላቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተገቢው ጊዜ ተቃውሞውን በተመለከተ ለኢራን ሕዝብ መግለጫ እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ኢራን ትላንት ምሽት ላይ 9 ሰዎች ሲገደሉ ይህም አጠቃላይ የሟቾቹን ቁጥር 22 አድርሶታል።

ማሻድ በተባለች ከተማ ባለፈው ሀሙስ የዋጋ ማሻቀብንና ሙስናን በመቃወም የተጀመረው የሕዝብ እንቅስቃሴ ወደ አጠቃላይ ጸረ አገዛዝ ተቃውሞ ተሸጋግሯል።

እስካሁን በመዲናይቱ ቴህራን ብቻ ወደ 450 የሚሆኑ ሰዎች መያዛቸውን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሃኒ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ በቲውተር ገጻቸው ተቃዋሚዎቹን ማበረታታቸውን ነቅፈዋል።

ትራምፕ ዛሬ በቲውተር ገጻቸው ኢራናውያን በስተመጨረሻ ጨካኝና በሙስና የተጨማለቀውን አገዛዝ እየተገዳደሩት ነው ሲሉ አስፍረዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለትራምፕ በሰጠው ምላሽ ፕሬዝዳንቱ ትኩረታቸውን በአሜሪካ በተራቡና መጠለያ ባጡ ሰዎች ላይ ቢያደርጉ ይሻላል ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሮሃኒ ተቃውሞውን በተመለከተ የተቆጠበ አስተያየታቸውን ሰተዋል።

ተቃውሞው መልካም አጋጣሚ እንጂ የሚያስፈራ ጉዳይ አይደም ብለዋል።

በሀገሪቱ ባለው የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ሰዎች አደባባይ ወተው መቃወማቸው ችግር የለውም፣ሕግ የሚጥሱትን ግን እንቀጣለን ብለዋል ሮሃኒ።

የ2009 ምርጫን ተከትሎ ከተነሳው ብጥብጥ ወዲህ በኢራን ተቃውሞ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው።

በ2009ኙ ተቃውሞ የ30 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።

በዚህ በአሁኑ ተቃውሞ ኢራናውያን ስራ አጥነትን፣የዋጋ ግሽበትንና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ድቀትን በማውገዝ ሰልፍ ወጥተዋል።

አንዳንዶቹ ግን የሀገሪቱን መሪዎች ማውገዝ መጀመራቸውን ሀገሪቱ ከ1979 የኢራን አብዮት በፊት ወደነበረው ንጉሳዊ አስተዳደር ትመለስ ማለታቸው ተቃውሞውን የፖለቲካ ገጽታ እንዲኖረው አድርጎታል።