ፖለቲከኞችና ሌሎች እስረኞች እንዲፈቱ ተወሰነ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 25/2010)

በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችና ሌሎች እስረኞች እንዲፈቱ መወሰኑን ኢሕአዴግ አስታወቀ።

የማዕከላዊ ምርመራ ወህኒ ቤትም ወደ ሙዚየምነት እንደሚቀየር ይፋ ሆኗል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እስረኞቹ መቼ እንደሚፈቱ እንዲሁም እነማን እንደሆኑ አልተገለጸም።

በመንግስትና በፓርቲ መገናኛ ብዙሃን እንደተገለጸው አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በጋራ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ መስማማታቸው ተመልክቷል።

በዓቃቢ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ፣ የተፈረደባቸው የተለያዩ ፖለቲከኞችና ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሐገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወስኗል።

በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተለፈፈው ዜና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ጭምር ትኩረት የሳበ ሆኖ ተገኝቷል።

ቢቢሲን ጨምሮ አንዳንድ አለምአቀፍ መገናኛ በዙሃን የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉም የፓለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ወሰነ ሲሉ ዘግበዋል።

ሆኖም በመንግስት መገናኛ ብዙሀን የተላለፈው ዜና እነማንና በምን ወንጀል የተከሰሱ እንደሚፈቱ በገልጽ አላስቀመጠም።

እስረኞችን ለመፍታት ወሳኔ ላይ መደረሱን የሚገለጸው ዜና የኢሃዴግ ስራ አስፈጻሚ ካወጣው መግለጫ ጋር የሚጣጣም ሆኖ አለመገኘቱ ወሳኔው ድንገተኛና ያልተጠበቀ አድረጎታል።

መግለጫውን ተከትሎ በውሳኔው ደስታቸውን የገለጹ፣ጥርጣሬያቸውን ያሰፈሩና ዋናውን ችግር አልነኩትም በሚል አስተያየታቸውን የሰጡ በማህበራዊ መደረኮች ታይተዋል።