ተቃውሞዎች ሲደረጉ ዋሉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 25/2010)በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተቃውሞዎች ሲደረጉ መዋላቸው ተገለጸ።

የኢህአዴግ መግለጫ ቅዳሜ ከወጣና ዛሬም የእስረኞች እንደሚፈቱ ከተገለጸ በኋላም የህዝብ ተቃውሞ የቀጠለ መሆኑ ታውቋል።

በምዕራብ አርሲና በምዕራብ ሸዋ ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ ተሰምቷል።

በአዳማ ጎሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው ታውቋል።

በወለጋ አሰንዳቦም አገዛዙን በመቃወም ህዝቡ አደባባይ መውጣቱን መረጃዎች አመልክተዋል።

ምዕራብ አርሲ ከሻሸመኔ ጀምሮ ያሉት አካባቢዎች ያለው ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

በኮፈሌና አርሲ ኮኮሳ ግጭትን ያስከተሉ ተቃውሞዎች መደረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በአጋዚ ሰራዊትና በህዝቡ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ መቀጠሉን የገለጹት ምንጮች ህዝቡ በቁጣ እያደረገ ያለው ተቃውሞ እየጠነከረ መምጣቱ ነው የተገለጸው።

በምዕራብ ሸዋ አምቦና ባኮም ተመሳሳይ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዳለ ይነገራል።

በአዳማ ዩኒቨርስቲ 18 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት መቀጣታቸውን ተከትሎ የጎሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ታውቋል።

የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ያነጣጠረው የአዳማ ዩኒቨርስቲው ጥቃት ያስቆጣቸው ተማሪዎች ተቃውሞቸውን በመግለጽ በአስቸኳይ የተባረሩት ተማሪዎች እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

በቅርቡ በአዳማ የእግር ኳስ ውድድር ለማድረግ ለመጣው የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድን ደማቅ አቀባበል መደረጉ ያስቆጣው አገዛዙ የአጋዚ ሰራዊቱን በማሰማራት የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ወከባ ሲፈጽም መቆየቱን መዘገባችን የሚታወስ ነው።

የጎሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በህወሀት አገዛዝ ላይም ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ታውቋል።

በአሰንዳቦም ዛሬ ተቃውሞ መደረጉ የታወቀ ሲሆን በህወሃት መንግስት ላይ ውግዘት ቀርቧል።

በወለጋ በተለያዩ አካባቢዎችም ህዝባዊ ተቃውሞ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል። ኢሳት ያነጋገራቸው የኦፌኮ አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ እንደሚሉት በየቦታው ያለው ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል። በቋፍ ነው ያለው።

በሌላ በኩል በአማራና በቤንሻንጉል የወሰን አካባቢዎች በተለይ በጃዊ እና ዳንጉር ወረዳ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ለመቆጣጠር የወረዳና የዞን የአስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ፣ ከምዕራብ ዕዝ ክፍለጦሮች አመራሮች ቡድን ጋር በዳንግላ ከተማ ስብሰባ መቀመጣቸው ታውቋል።

በወሰን አካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር መባባሱን ተከትሎ የህወሀት አገዛዝ ከቁጥጥር እንዳይወጣ ስጋት ውስጥ መግባቱ ይነገራል።