(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 23/2010)
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ያወጣው መግለጫ ሕዝብን ለማታለል ያለመና ከዚህ ቀደም ካወጣቸው መግለጫዎች የተለየ አለመሆኑን አስተያየታቸውን ለኢሳት የሰጡ ምሁራንና ፖለቲከኞች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ የኢሕአዴግ አመራር ሙሉ ሃላፊነትን እወስዳለሁ ሲል በመግለጫው ማስፈሩ ከቃላት ጋጋታ ያልዘለለ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እናም ሕዝቡ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል ለነጻነት የተጀመረውን ጉዞ ማፋጠን ያስፈልጋል ብለዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጥሩነህ ገምታ ለኢሳት እንደገለጹት “የኢሕአዴግ መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቀውስ የሚፈታ ሳይሆን የሚያባብስ ነው።”
መግለጫውም ገዢው ፓርቲ ከሕዝብ የተነጠለ መሆኑን ከማብራራት ያለፈ ስለመፍትሄው ያለውም ነገር የለም ብለዋል።
እንዲያውም ሕዝቡ ለመብቱ የሚያካሂደውን ትግል በሃይል ለመቸፍለቅ መዛቱን ነው የተናገሩት።
በአሜሪካ አንዲኮት ኮሌጅ የአለም አቀፍ ህግና የሰብአዊ መብት መምህር ዶክተር ሰማህኝ ጋሹ በበኩላቸው የኢሕአዴግ መግለጫ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ብለዋል።
ምክንያታቸውን ሲገልጹም ኢሕአዴግ ላለፉት 26 አመታት ተመሳሳይ መግለጫ አውጥቶ በተግባር ግን የተለየ ለውጥ የለም ነው ያሉት።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ቀውስ ሙሉ ሃላፊነቱ የአመራሩ እንደሆነ ይገልጻል።
በሀገሪቱ ለተከሰተው ማንኛውም ጉዳትም ሕዝቡንና አባላቱን ይቅርታ እስከመጠየቅ ደርሷል።
ይህ አባባል ግን በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት መነሻ ሊሆን እንደሚችል ምሁራን ይናገራሉ።
የሕግ ባለሙያው ዶክተር ፍጹም አቻምየለህ ለኢሳት እንዳሉት ይህ አገላለጽ በውስጣቸው ያለውን መከፋፈል ለመሸፋፈን የተጠቀሙበት ዘዴ ነው።
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው ከቃል ይልቅ ተግባር ካልቀደመ የቃላት ጋጋታ ምንም አይጠቅምም ነው ያሉት።
እናም አዲስ ነገር በሌለበትና የታሰሩት የሕሊና እስረኞች ሳይለቀቁ ስለለውጥ ማውራት አይቻልም ብለዋል።
ሁሉም አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ እውነተኛ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ሕዝቡ ትግሉን ሲያጠናክርና ለነጻነት የሚያደርገውን ጉዞ በተፋጠነ ሁኔታ ሲቀጥል ብቻ ነው።