የፈረንጆቹ 2017 ሊጠናቀቅ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 20/2010) የፈረንጆቹ 2017 እሁድ ይጠናቀቃል።

እንደ ሌሎቹ አመታት ሁሉ 2017 ታላላቅ ክንዋኔዎችን አስተናግዷል።

አመቱ የፖለቲካ፣የኢኮኖሚ፣የሽብር፣የተፈጥሮ አደጋ፣የኒዩክለር ፍጥጫ።አሰቃቂ ጦርነቶችና ሌሎችም ክስተቶች ተከናውነውበታል።

አሮጌ አመት ባለፈ ቁጥር እንዲህ አይነት ለየት ያለ አመት እስካሁን አልነበረም ማለት የተለመደ ነው።

የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመትም በርካታ መጥፎና ጥሩ ክንውኖችን በማስተናገዱ ለየት ያለ አመት ሆኖ አልፏል የሚሉ በርካቶች ናቸው።

ከአፍሪካ ብንጀምር በዚምባቡዌ ሮበርት ሙጋቤ ከ37 አመታት በኋላ ከስልጣን ተወግደዋል።

እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ የነጮችን አገዛዝ ለመጣል በመታገላቸው በእስር የማቀቁት ሙጋቤ ዲሞክራሲ ማለት ስልጣንን ለሌላ ባለተራ ማስተላለፍን የሚጨምር መሆኑን ግን የተገነዘቡ አይመስልም።

ወታደራዊው ሃይል መገናኛ ብዙሃንን ተቆጣጥሮ የቁም እስረኛ ሲያደርጋቸው ስልጣኔን በፍቃዴ ለቅቄያለሁ ብለው ዘወር ብለዋል።

የአለም ድንቁ እግር ኳስ ተጫዋች የነበረው ላይቤሪያዊው ጆርጅ ዊሃ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ያሸነፈው በዚሁ እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ አመት ነው።

በእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት እየተደረገ ያለው ሂደት በሀገሪቱ የፖለቲካ ምስቅልቅልን አስከትሏል።

በ2016 የተደረገው ከሕብረቱ የመልቀቅ ህዝበ ውሳኔ ገና በሂደቱ ጅማሬ እንጂ ዋናው ጉዳይ የነበረውና ሀገሪቱ ህብረቱን የምትለቅበትን ድርድርና ቅድመ ሁኔታ የተመልከተው ጉዳይ በተጠናቀቀው አመት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአስቸኳይ ምርጫ እንዲጠሩ አስገድዷቸው ነበር።

ምርጫው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ፓርቲያቸው የነበረውንም አብላጫ ወንበር አጥቶ ከተቀናቃኛቸው ጋር እኩል የፓርላማውን ወንበሮች ተጋርተዋል።

በማይናማር በሮሒንጂያ ሙስሊሞች ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ በአለም ላይ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከተደረጉ በደሎች ሁሉ ዘግናኙ ተብሎ ተመዝግቧል።

በዚህም ድርጊት 9ሺ ያህል ሰዎች ሲገደሉ 6 መቶ 50 ሺ ያህል ዜጎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

በ2014 ሞሱልን ተቆጣጥሮ አለምን ያስደነገጠው አይሲስ በአሜሪካና አጋሮቿ በሚመራው ጥምር ሃይል ባለፈው ሰኔ ከሞሱል ሙሉ በሙሉ ተወግዷል።

ከተማይቱም ከሶስት አመታት ጦርነት በኋላ ነጻ ወጥታለች።

ያስከፈለው ዋጋ ግን ከባድ ነበር።

ወደ 40ሺ የሚጠጉ ሰላማዊ ሰዎች ሲያልቁ አንድ ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ተፈናቅለዋል።

በሳውዳረቢያ ለውጥ አራምጁ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ባለፈው ሰኔ ልኡል ሆነው ከተሾሙ በኋላ ራዕይ 2030 በሚል የኢኮኖሚና ማህበራዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል።

በሀገሪቱ መንግስት ቁጥጥር ስር ያለውን የነዳጅ ሞኖፖሊ በሕዝብ አክሲዮን እንዲያዝ ማቀዳቸውና ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ የሚፈቅደው እቅዳቸው ተጠቃሽ ነው።

በኢትዮጵያ ትልቅ የኢኮኖሚ ድርሻውን የተቆጣጠሩትን ሼክ መሀመድ ሁሴን አላሙዲንን ጨምሮ ከ2 መቶ በላይ የሳውዲ ልኡላንና ነጋዴዎችን በሙስና ጠርጥረው ጠራርገው በሆቴል ማጎራቸው ሳይጠቀስ  የሚታለፍ አይደለም።

በአለም ያለው አጠቃላይ ኢኮኖሚ መሻሻልም ተጠቃሽ ነው።

አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ ኢንቨስትመንት፣ንግድና የኢንደስትሪ ምርት በ2017 እድገት ማሳየቱ ይነገራል።

አጠቃላይ የለም ኢኮኖሚ በ2017 3 ነጥብ 6 በመቶ አድጓል ይላል የገንዘብ ተቋሙ ።

የአለም የሙቀት መጠን መጨመር እየቀጠለ እንደሆነ በሙያው የተሰማሩ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

ከፍተኛው ሙቀት የተመዘገበው በ2016 ቢሆንም ዘንድሮ ሙቀቱ ከሌሎች አመታት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪን አሳይቷል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህንን የተመራማሪዎች ምክር ከማይቀበሉት አንዱ ናቸው።

በሰሜን ኮሪያና በሌሎች ሀገራት መካከል የነበረው የኒዩክለር ፍጥጫም እየተጠናቀቀ ባለው አመትም ተባብሶ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ 6ኛውን የኒዩክለው ሙከራ ባለፈው መስከረም አድርጋለች።

ሙከራውን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳትን ዶናልድ ትራምፕም ሰሜን ኮሪያ ላይ እሳት እናዘንባለን ይህ አጭር ሰው ፕሬዝዳንቱን ኪም ጁንግ ኡንን ማለታቸው ነው በሮኬት መጫወቱን ቢያቆም ይሻላል ብለው ዝተዋል።

ሁሉንም ያሚያስማማውና በ2017 የአለማችንን ትኩረት የሳበው ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ “አሜሪካ ትቅደም” ብለው የአሜሪካንን የፕሬዝዳንትነት መንበር መረከባቸውና ሀገሪቱ የምትከተለውን የውጭ ፖሊሲ ለመቀየር መነሳታቸው ነው።

ትራንስ ፓስፊክ በመባል ከሚታወቀው የንግድ ውል እንዲሁም ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አሜሪካ እንድትወጣ ሲያደርጉ በቅርቡ ኢየሩሳሌምን የእስራኤል መዲና ነች ሲሉ እውቅና መስጠታቸውና የአሜሪካን ኤምባሲ ከቴላቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም አዞራለሁ ማለታቸው በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት እንዲያገረሽ ምክንያት ሆኗል።

አዲሱን የፈረንጆቹን አመት 2018ን የፊታችን ሰኞ ስንቀበል እንደቀደሙት አመታት ሁሉ አመቱ በመጥፎም ሆነ በጥሩ ክንዋኔዎች ሊሞላ እንደሚችል 2017 አመላካች ጉዳዮችን ይዟል።

የትራምፕ ውሳኔዎችም አንዱ ማሳያ ነው።