የዶክተር መረራ የክስ መዝገብ ሌላ ማስረጃ ቀረበበት

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 20/2010)

ብይን ይሰጥበታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የዶክተር መረራ ጉዲና የክስ መዝገብ ሌላ የቪዲዮ፣ የድምጽና የምስል ማስረጃ በአቃቢ ሕግ እንደቀረበበት ተሰማ።

ዐቃቢ ህግ ማስረጃውን ያቀረበው በዶክተር መረራ ላይ የማቀርበውን ማስረጃ ጨርሻለሁ ካለ በኋላ ነው።

ዶ/ር መረራም የቀረበው ማስረጃ የመንግስት ባለስልጣናት ይቅርታ የጠየቁብት ነው ሲሉ ተከራከረዋል።

ከአንድ አመት በለይ በእስር ላይ የሚገኙት ዶክተር መረራ ጉዲና ዛሬ ለውሳኔ ተቀጥረው ነበር ።

ነገር ግን ዐቃቢ ህግ አዲስ ነገር አግኝቻለሁ በሚል የቪዲዮ፣ የድምጽና የፎቶ ማስረጃዎችን ለፍርድቤት ማቅረቡ ታውቋል።

አቃቢ ህግ አገኘሁት ያለውን ማስረጃ የተመከቱት ዶክተር መረራ ጉዲና የቀረበብኝ ማስረጃ የመንግስት ባለስልጣናት ይቅርታ የጠየቁበት ነው በማለት ተናግረዋል።

ቄሶች፣አባ ገዳዎች እና ሽማግሌዎች ወደ ህዝብ ተልከው ህዝብን ያግባቡበት መሆኑንም አስታውሰዋል።

10 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ድንጋይ አትወርውሩብን በሚል መለማመኛ የቀረበበት ጉዳይ ማስረጃ ተብሎ መቅረቡ ትክክል አይደለም ሲሉ ዶክተር መረራ በጠበቆቻቸው አማካይነት ተቃውመዋል።

ማስረጃው ከተሰማ በኋላ ለውሳኔ ለታህሳስ 25 / 2010 መቀጠሩም ታውቋል።

የፍርድ ቤቱን ውሎ የተከታተሉት የኦፌኮ አመራር አባል አቶ ጥሩነህ ገምታ ለኢሳት እንደተናገሩት አቃቢ ህግ ማስረጃ ጨርሻለሁ ካለ በኋላ ማስራጃ አለኝ ብሎ መቅረቡ ከህግ አንጻር እንዴት እንደሚታይ የህግ ባለሙያዎች አሳብ ቢሰጡበት ጥሩ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ከዚህ ፍርድቤት ፍትህን እናገኛለን ብለን አንጠብቅም። በቅርቡ ግን ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍትህን እናገኛለን ብለዋል።

ዶክተር መረራ ጉዲና በአውሮፓ ህብረት ግብዣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለማስረዳት አውሮፓ ተገኝተው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ለእስር ተዳርገው በሽብር ወንጀል መከሰሳቸው ይታወሳል።

በርካታ የኦፌኮ የስራ አስፈጻሚ አባላትና ደጋፊዎች ለእስር ተዳርገው ይገኛሉ።

ሁሉም በተመሳሳይ ከዚህ ፍርድቤት ፍትህ እናገኛለን ብለን አንጠብቅም ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።

ለ5 ዓመታት ታስረው ከተለቀቁ በኋላ ዳግም ለእስር ተዳርገው ሁለት አመታት የሞላቸው የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ የጤናቸው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን መዘገባችን ይታወሳል።

የተሻለ ህክምና ማግኘት እንዳለባቸውና መድሃኒትም እንዲቀየርላቸው በጠበቆቻቸው አማካኝነት ቢጠይቁም ፍርድቤቱ ወህኒ ቤቱ እንዲከታተለው ከማለት ውጪ የወሰደው ርምጃ እንደሌለም ይታወቃል።