(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 12/2010)
በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ አንድ የአፍጋኒስታን ተወላጅ ሆን ብሎ በመኪና ባደረሰው አደጋ 19 ያህል ሰዎች መቁሰላቸው ታወቀ።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰአት ከደጋው ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ባይኖሩም በአደጋው ከቆሰሉት ሰዎች ግን አራቱ ሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
በሜልቦርን ማዕከላዊ የንግድ ክፍለ ከተማ ለገና ገበያ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የነበሩ ሰዎችን በሚያሽከረክረው ሱዙኪ ኤስ ዩ ቪ ተሽከርካሪ የገጨው የ32 አመቱ ትውልደ አፍጋኒስታናዊ መድሃኒት አላግባብ የሚወስድና የአእምሮ ችግር የነበረበት ነው ሲል ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊስ አክሎም ድርጊቱ ሆን ተብሎ የተፈጸመና የፈሪ ተግባር ነው ብሏል።
ድርጊቱ የፈጸመው ግለሰብና አንድ ፖሊስ እንዲሁም የአራት አመት ሕጻን ልጅ ከተጎጂዎቹ መካከል ናቸው።
የአራት አመቷ ሕጻን ጭንቅላቷን ክፉኛ መጎዳቷን የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ጉዳቱን የፈጸመው ግለሰብ ወዲያውኑ ሲያዝ በቦታው አደጋውን በካሜራ ሲቀርጽ የነበረ ሌላ ግለሰብ ደግሞ በቦርሳው ውስጥ ሶስት ቢላዎች በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ውሏል።
ሁለቱ ግለሰቦች ግን ግንኙነት አላቸው ብሎ እንደማያምን ፖሊስ ገልጿል።
ፒሊስ ድርጊቱ የተፈጸመው ሆን ተብሎ ነው ቢልም ግለሰቡን ለጥፋት ምን እንዳነሳሳው ወይም ከሽብር ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ግን እስካሁን ማወቅ አልተቻለም ብሏል።
ባልፈው ጥር ወር የዛሬው ጥቃት በተፈጸመበት አቅራቢያ በተሽከርካሪ በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት 6 ሰዎች ሲሞቱ አደጋውን ያደረሰው ግለሰብ የአእምሮ ህመመተኛ ነው በሚል በሽብርተኝነት ወንጀል ሳይከሰስ ቀርቷል።