(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 11/ 2010)
ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ በርካታ ዜጎች ሲገደሉ ድምጹን ያላሰማውና በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የትግራይ ተወላጆች ማህበር በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለተገደሉ ዜጎች የሀዘን መግለጫ ማውጣቱ ተሰማ።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በመከላከያ ሰራዊት፣ በፊደራል ፖሊስና በልዩ ሃይል ፓሊስ ሲገደሉ ድምጹን ያላሰማው ማህበር አሁን ላይ አለሁ ማለቱ በብዙዎች ዘንድ እንዲተች አድርጎታል።
በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የትግራይ ተወላጆች ማህበር በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለተገደሉ ዜጎች በተለየ ሁኔታ የሃዘን መግለጫ ማውጣቱ ብዙዎችን ያስገረመና ለጥያቄ የጋበዘ ሆኗል።
ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ በጋራ እንሰራለን የሚለው የማህበሩ መግለጫ የተፈጸመውን ግድያ ኋላ ቀርና አስነዋሪ በማለትም ይኮንናል።
የማህበሩን መግለጫ የተመለከቱ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ በርካታ ዜጎች በመከላከያ ሰራዊት፣ በፊደራል ፖሊስና በልዩ ፓሊስ ተገድለዋል።
በተለይም በ2009 በኢሬቻ በዓል ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ለተገደሉትና ከ600 በላይ ስለ ሚሆኑት ዜጎች ማህበሩ ያለው ነገር የለም በማለት ተዝብታቸውን ያስቀምጣሉ ።
በሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የሚመራውና የህወሃት ጄኔራሎች ከጀርባ እንዳሉበት የሚጠቀሰው የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን ሲገድልና ሲያፈናቅል በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን ሲያሰሙ ይህ ማህበር ትንፍሽ አላለም ሲሉም ያክላሉ።
ታዲያ በልዩ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ላይ ለተፈጸመው ግድያ መግለጫ ማውጣቱ ምክንያቱ ምንድነው ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ማህበሩ የህወህትን አጀንዳ እንደሚያራምድ ማሳያ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በተደጋጋሚ እንደሚታየው በሀገሪቱ በሚፈጥሩ ግጭቶች የሁለቱ ክልሎች እርስ በእርስ መደጋገፍ በተደጋጋሚ ተስተውሏል።
ከአማራ ክልል ተፈናቅልዋል ለተባሉ የትግራይ ተወላጆች የሶማሌ ክልል የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ለተከሰተው የድርቅ አደጋ የትግራይ ክልል በልዩ ሁኔታ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የዚህ ማህበር ድርጊትም ከዚህ የተለየ አይደለም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች ህወሀት የሶማሌ ክልልን በጉያው አቅፎ የፓለቲካ ቁማር እየተጫወተ ነው ሲሉ የተቻሉ።
መግለጫው በማጠቃለያውም ከተለያዩ ህዝባዊ አደረጃጀቶችና ተቋማት ጋር በመሆን ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ይሰራል ብሏል። በምን መልኩ የተለየ ትኩረት እንደሚሰጥ ግን ያለው ነገር የለም።