የሱዳን ጦር የሀገራችንን ድንበር መጣሱ አለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታሕሳስ 11/2010)

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የሱዳን ጦር የሀገራችንን ድንበር በመጣስ በቅርቡ የፈጸመው ወረራ አለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር ነው ሲል ለፕሬዝዳንት አልበሽር በጻፈው ደብዳቤ አሳሰበ።

የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣም ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ለሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ይህን መሰል ደብዳቤ ሲጽፍ የመጀመሪያው አይደለም።

የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን ተላልፎ ተሰቷል ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ጉዳዩ ያሳሰበው መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

አሁን ለፕሬዝዳንት አልበሽር የተጻፈውና ለተባበሩት መንግስታት እንዲሁም ለአፍሪካ ህብረት በግልባጭ የተገለጸው ደብዳቤ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ይጠይቃል።

እንደ ኮሚቴው ደብዳቤ ገለጻ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ተላልፎ ወረራ መፈጸሙ አለም አቀፍ ህግን የሚጻረር ነው።

የአንድን ሉአላዊ ሀገር ድንበርን ተሻግሮ መግባትና በሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረስ የተባበሩት መንግስታትን ቻርተር ይጥሳልም ነው ያለው የኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ ኮሚቴ።

እናም የፕሬዝዳንት አልበሽር መንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ የኢትዮጵያን ድንበር በመጣስ የሚያደርገው ወረራ ሊቆም እንደሚገባ አሳስቧል።

በኮሚቴው ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው የሕወሃት አገዛዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ያላገኘ በመሆኑ ማንኛውም ከሱዳን ጋር የተገባ ቃልም ሆነ ስምምነት ተቀባይነት ያለው ጉዳይ አይደልም።

እንደ መግለጫው የሕወሃት አገዛዝ በሱዳንና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለውን የቆየ መልካም ግንኙነት ሆን ብሎ እያበላሸው ይገኛል።

ምንም እንኳን ሕወሃት ከሱዳን መንግስት እገዛ በማግኘት ለስልጣን ቢበቃም የኢትዮጵያን ድንበር ለጥቅሙ ሲል አሳልፎ መስጠቱ ወንጀለኛ ያደርገዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ የድንበር ኮሚቴ ለሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በላከው ደብዳቤ።

የሱዳን ጦር በተደጋጋሚ ጊዜ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ሲገባ በዝምታ የሚመልከተውም በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቅ ከሱዳን መንግስት ጋር ሕወሃት በፈረመው ስምምነት መሰረት እንደሆነም ገልጿል።

እናም የሱዳን መንግስት ከሕወሃት ጋር የተፈራረመው ስምምነት የኢትዮጵያን ሕዝብ የማይወክል በመሆኑ ጦሩን በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንዲያስወጣ ኮሚቴው በደብዳቤው ጠይቋል።

በኢትዮጵያና ሱዳን አጎራባች ባሉ አርሶ አደሮች ላይ የሚደርሰው በደልም ሊቆም እንደሚገባ የኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ለሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በጻፈው ደብዳቤ አመልክቷል።