ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደረገለት

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2010)

የጎንደሩ ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በኦሮሚያ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደረገለት።

የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የፋሲል ከነማን ተጫዋቾች “ፋሲል ኬኛ” በማለት በሞተረኛ ፖሊሶች አጅበው ፍቅራቸውን በመለገስ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋቸዋል።

የአዳማ ከነማ ህዝብ ለፋሲል ከነማ ያደረገው አቀባበል በኦሮሚያና አማራ ሕዝብ መካከል ያለው ትስስር ጠንካራ መሆኑን አመላክቷል።

የሕወሃትን አገዛዝ በመቃወም በአንድ ወቅት የጎንደርና የባህርዳር ህዝብ የኦሮሞ ደም ደሜ ነው ማለቱን ተከትሎ በኦሮሚያ ተመሳሳይ ምላሽ መሰጠቱ ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ልዩነት ሳይሆን አንድነት ያላቸው ማህበረሰቦች እንደሆኑ አስመሰከሩ።

የጣና እምቦጭ አረም የሃይቁን ሕልውና አደጋ ላይ ሲጥለውም የኦሮሞ ወጣቶች “ጣና ኬኛ” በማለት ወደ አካባቢው የተመሙት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ባስደመመና ባስገረመ ሁኔታ ነበር።

በአንድ ወቅት እሳትና ጭድ ናቸው ተብለው በቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር በአሁኑ የሕወሃት የስራ አስፈጻሚ ጌታቸው ረዳ የተፈረጁት የኦሮሚያና የአማራ ክልል ነዋሪዎች በደም የተሳሰረ አንድነት ያላቸው መሆናቸውን በተለያዩ ድርጊቶች አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻ በማድረግ በስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ግጭቶች እየተካሄዱ በተለይ በትግራይ ክለቦችና በአማራ ክለቦች መካከል የዘር ፖለቲካው ያስከተለው መቃቃር ለሰዎች መገደል ምክንያት ሆኗል።

አሁን የተሰማው የአዳማ ነዋሪዎች ለጎንደሩ ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ያደረጉት አቀባበል እጅግ ደማቅና ማራኪ ነበር።

የደሴና ኮምቦልቻ ሕዝብም በተመሳሳይ ሁኔታ ለነቀምት ከነማ ቡድን ተመሳሳይ አቀባበል ማድረጉ ይታወሳል።

በኦሮሚያ ክልል የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች በፖሊስ ሞተር ታጅበው “ፋሲል ኬኛ” እያሉ ጨፍረዋል።

በዝማሬያቸውም ለአማራ ሕዝብ ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል።

ይህም ደማቅ አቀባበል ለአማራና ኦሮሞ ሕዝብ አንድነት መጠናከር የፍቅር ድልድይ ሆኖ ትስስሩን እያጠናከረው መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ይህ ፍቅር ደግሞ በሌሎችም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተምሳሌት ሆኖ ሁሉንም ዜጋ የሚያስተሳስር እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል።