ሲሪል ራምፖሳ አሸነፉ  

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2010)

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ/ኤ ኤን ሲ/ ፓርቲን የመሪነት ቦታ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሲሪል ራምፖሳ አሸነፉ።

የመሪነቱን ቦታ ማን ይወስዳል የሚለውን ውጤት ለማወቅ ደቡብ አፍሪካውያን በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።

አዲሱ ተመራጭ ሲሪል ራምፖሳ በስልጣን ላይ ያሉትን የሀገሪቱን ፕሬዝዳንትና የፓርቲውን መሪ ጃኮብ ዙማን ይተካሉ።

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ የኤ ኤን ሲ ፓርቲ መሪን ለመምረጥ በተካሄደው ምርጫ በምክትል ፕሬዝዳንቱ ሲሪል ራምፖሳና በቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኮሳዛና ደላሚና ዙማ መካከል ከፍተኛ ፉክክር መደረጉን ነው መረጃዎች ያመለከቱት፡፡

5ሺ የሚሆኑ ተወካዮች ድምጽ የሰጡበት ይህ ምርጫ ላለፉት 23 አመታት በደቡብ አፍሪካ በስልጣን ላይ ያለውን የኤ ኤን ሲ ፓርቲ መሪ ለመምረጥ ነው።

እናም በውጤቱ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሲሪል ራምፖሳ ማሸነፋቸው ይፋ ሆኗል።

አሸናፊው ራምፖሳ በመጪው የፈረንጆቹ አዲስ አመት በሀገሪቱ ለሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጠንካራ ተወዳዳሪ ይሆናሉ የሚል እምነት ተጥሎባቸዋል።

ነገር ግን የአሁኑ የፓርቲው ምርጫ ከፍተኛ ሽኩቻ የታየበት መሆኑ ደግሞ ሌላ ጥያቄን ጭሯል።

ይህ ደግሞ የ2019ኙ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ፓርቲውን እንዳይሰነጥቀው የሚል ስጋትንም ፈጥሯል።

በድምጽ አሰጣጡ ወቅት ተወካዮቹ ሃይለቃል ሲለዋወጡ እንደነበርም ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

በአውሮፓውያኑ 1991 አፓርታይድ ከደቡብ አፍሪካ ሲወገድ ከ1994 ጀምሮ በተደረጉ ምርጫዎች የኤ ኤን ሲ ፓርቲ በከፍተኛ ድምጽ እያሸነፈ ይገኛል።

በአውሮፓውያኑ ከ1994 እስከ 1999 ታዋቂው የጸረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በፓርቲው መሪነትና በሀገሪቱ በፕሬዝዳንትነት ማገልገላቸው ይታወሳል።

የአሁኑ ምርጫ አንደኛ እጩ የሆኑት የአሁኑ ፕሬዝዳንት የቀድሞ ባለቤትና የቀድሞ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ደላሚኒ ዙማ ነበሩ።

አንጋፋ ፖለቲከኛ የሆኑት ደላሚኒ ዙማ በደቡብ አፍሪካ በነጮች የተያዙ የንግድ ተቋማት በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ያላቸውን ተጽእኖ እንዲሁም በሀገሪቱ ያለውንና በነጮችና በጥቁሮች መካከል የሚታየውን ከፍተኛ የሀብት ልዩነት አጥብቀው ይነቅፋሉ።

በማንዴላ አስተዳደር ወቅት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት የ68 አመቷ ደላሚኒ ዙማ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ሲጋር እንዳይጨስ በመከልከላቸው ይታወቃሉ።

ደላሚኒ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትም አገልግለዋል።

ሌላኛው እጩ ሆነው የቀረቡትና አሁን የአሸናፊነት መንበሩን የተቆናጠጡት ሲሪል ራምፓሳ ናቸው።ራምፖሳ በሀገሪቱ ካሉ ቱጃሮች አንዱ ሲሆኑ የሰራተኛ ማህበራት መሪም ነበሩ።

ወደ ንግዱ አለም ከመግባታቸው በፊት በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ አፓርታይድን ለማስወገድ ድርድር በተደረገበት ወቅትም ዋና ተደራዳሪ ነበሩ።

የ65 አመቱ ራምፖሳ ሙስናን ለማጥፋት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደገና ለማጠናከር እሰራለሁ ብለዋል ከምርጫው በፊት ።

የመሪነቱን ቦታ የጨበጡት ራምፖሳ የገቡትን ቃል ስለመፈጸማቸው ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ይሆናል ብሏል ዘገባው።

ነገር ግን የአሁኑ የምርጫ ሂደት በአደጋ ላይና በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ተብሎ በፓርቲው መሪዎች ጭምር ለሚነገርለት ኤ ኤን ሲ ወሳኝ ነው ተብሏል።

ምርጫውን ባሸነፉት ራምፖሳ ላይም ትልቅ የቤት ስራ ወድቋል ነው የተባለው።

ባለፈው አመት በተደረገው የክልል ምርጫ ፓርቲው በ54 በመቶ ብቻ ማሸነፉ ሕዝቡ በፓርቲው ደስተኛ አለመሆኑን ያመላክታል ብለዋል ስልጣን ለቃቂው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ።