(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2010)
በምዕራብ ሀረርጌ በድሮሎቢ ወረዳ በጋድሌ ቀበሌ የተገደሉት እስከ አንድ መቶ የሚደርሱ የሶማሌ ክልል ተወላጆች በኦሮሚያ ፖሊስ ስር ተጠልለው የነበሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
አቶ ሃይለማርያም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ድንገት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በኦሮሚያና ሶማሌ ክልልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቱ አገርሽቶ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል።
መከላከያና የጸጥታ ሃይሎች ወደ አካባቢው የገቡት ግን ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው በአካባቢው በተሰነዘሩ ጥቃቶች 29 ኦሮሞዎች ተገድለዋል።
ከ360 በላይ መኖሪያ ቤቶችም ከነሙሉ ንብረታቸው ተቃጥለዋል ብለዋል።
በሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ጅምላ ግድያና መፈናቀል እስካሁን አለመቆሙን የሚያረጋግጥ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ሰሞኑን ተከስቷል።
በዚሁ አካባቢ እርስ በርስ ከሚካሄደው ግጭት በተጨማሪ በመከላከያ ሰራዊት የሚፈጸመው ግድያም በርካታ መሆኑ ነው የሚነገረው።
ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ በሕወሃት/ኢሕአዴግ የሚመራው አገዛዝ እስካሁን ተጠያቂ ያደረጋቸው አካላት በይፋ አልተገለጹም።
በተለይም በአመራር ደረጃ ያሉት አይነኬ ናቸው።
በሰሞኑ የምዕራብ ሀረርጌ ድሮሎቢ ወረዳ ጋድሌ ቀበሌ ግጭት እስከ 1 መቶ የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል።
የአካል ጉዳት ደርሷል፣ሀብትና ንብረትም ወድሟል።
ይህንኑ አስመልክቶ ድንገት መግለጫ የሰጡት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ታዲያ ግድያው የተፈጸመው በኦሮሚያ ፖሊስ ጣቢያ በተጠለሉ ሰዎች ላይ ነው ብለዋል።
ይህ አባባላቸው ታዲያ አካባቢውን ጥሎ የወጣው የመከላከያ ሰራዊት ሆን ብሎ ያቀነባበረው ነው ከሚለው ጋር የሚጋጭ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የመከላከያ ሰራዊቱና የጸጥታ ሃይሉ በአካባቢዎቹ የተሰማሩት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
ይህም አቶ ለማ የመከላከያ ሰራዊቱ ጣልቃ እንዲገባ ሳንጠይቀው ገብቷል ካሉት ጋር ተቃራኒ መግለጫ ሆኗል።
ታዛቢዎች እንደሚሉት አቶ ሃይለማርያም ተጠያቂ ማድረግ የፈለጉት የኦሮሚያ ፖሊስን ነው።
አቶ ሃይለማርያም ይህን ይበሉ እንጂ የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ግን በሶማሌዎች ላይ ግድያ የፈጸመው መጀመሪያ በኦሮሞች ላይ በሀዊ ጉዱና ወረዳ ከታህሳስ 5 ጀምሮ ጥቃት ስለተፈጸመ ነው።
እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ በዚሁ ስፍራ ኢብሳና ታኦ በሚባሉ ቀበሌዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት 20 ኦሮሞዎች ተገድለዋል።
ከ360 በላይ መኖሪያ ቤቶችም ወድመዋል።በዚሁ ጥቃት የተበሳጩት የኦሮሚያ ተወላጆች ታዲያ በሃዊ ጉዲና ወረዳ 32 የሶማሌ ተወላጆችን ገድለዋል ነው ያሉት።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ካልተገታ እንደ ሀገር አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሊጥለን ይችላል ብለዋል።
አቶ ሃይለማርያም በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ባለው ግጭትም ተማሪዎች መሞታቸው አሳሳቢና አሳዛኝ መሆኑን ነው የገለጹት።
በሀገሪቱ ያለውን ቀውስ በተመለከተ መረጃን የሚያሰራጩ አካላት ሃላፊነት እንደሚወስዱም ማስጠንቀቂያ ሰተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የዚህ ሁሉ ቀውስ ምክንያት ርሳቸው የሚመሩት አገዛዝ ስለመሆኑ ግን የገለጹት ነገር የለም።