የተጀመሩት ተቃውሞዎች እንደቀጠሉ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2010)

በድሬዳዋ ዩንቨርስቲ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።

ዛሬ በዩኒቨርስቲው ተማሪዎች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የአጋዚ ሰራዊት ወደ ግቢው በመግባት ድብደባ የፈጸመ ሲሆን በርካታ ተማሪዎች ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ዛሬ ተቃውሞ መደረጉ ታወቀ።

በአማራ ክልል ትምህርት በተቋረጠባቸው ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት አልተጀመረም።

በደብረማርቆስ ፣ደብረታቦር ፣ባህርዳርና ወልድያ ዩኒቨርስቲዎች አብዛኛው ተማሪ ወደየቤተሰቡ መሄዱ ታውቋል።

በሌላ በኩል ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተባባሰውን የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የመከላከያ ሰራዊት እየገባ መሆኑ ታውቋል።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ የተነሳው ተቃውሞ በመላ ሀገሪቱ በዩኒቨርስቲዎች ለተጀመሩት እንቅስቃሴዎች አጋርነትን ለማሳየት እንደሆነ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ተማሪዎቹ በተለይ በአዲግራት በኦሮሞና አማራ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያና ድብደባ በማውገዝ በግቢያቸው ውስጥ የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት የጀመሩ ሲሆን ተቃውሞውም እየተስፋፋ መሄዱም ታውቋል።

የአጋዚ ሰራዊት ወደ ዩኒቨርስቲው ዘልቆ በመግባት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞዎችን እያሰሙ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ርምጃ መውሰዱ ተገልጿል።

ከ10 በላይ ተማሪዎች ተጎድተው ድል ጮራ ሆስፒታል መግባታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

የአጋዚ ሰራዊት የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች እየለየ ጥቃት መፈጸሙን የጠቀሱት ምንጮች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ተማሪዎችም ታስረው መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የዘንዘልማ ካምፓስ ተማሪዎች ዛሬ ተቃውሞ ከማስነሳትም አልፈው እስከ ብአዴን ቢሮ ድረስ በመሄድ ህወሃትን ደህና ሁን ጊዜህ ተጣናቋል ሲሉ ተሰናብተውታል።

የከተማዋ ነዋሪዎችም ከተማሪዎቹ ጋር በመሆን የኢህአዴግን ስልጣን ማክተም በማወጅ ስንብት አድርገውለታል።

የጨለንቆው ጭፍጨፋ ያስነሳው ተቃውሞ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ዛሬ በኢሉባቡር መቱ ከተማ የመቱ መምህራን ማሰለጠኛ ተቋም መምህራንና ሰራተኞች ጭፍጨፋውን በማውገዝ ተቃውሞ ማድረጋቸው ታውቋል።

በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናትና የከተማው ፖሊስ አባላት መሳተፋቸው ተገልጿል።

ተማሪዎቹና መምህራን በቅርቡ በጨለንቆ ለተገደሉትና በእስካሁንም በመከላከያ ሰራዊት በቀጥታ ህይወታቸውን ላጡት የኦሮሞ ተወላጆች በዝምታና እጃቸውን ጭንቅላታቸው ላይ በማድረግ ሀዘናቸውን መግለጻቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በቁጥር 311 ለሚሆኑትና በመከላከያ ሰራዊት እጅ ለተገደሉት ሰዎች 311 ሻማዎችን በማብራት ሀዘናቸውን የገለጹት የመቱ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተማሪዎችና መምህራን በጭፍጨፋው እጃቸው ያለበት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ትዕዛዙን የሰጡ የመንግስት ባለስልጣናት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል በመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪዎች የሚደረገውን የኮንትሮባንድና የእርዳታ እህል ሽያጭ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች በማስቆም ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው።

በቢሾፍቱ ደብረዘይት የመከላከያ ሰራዊት ኦራል ተሽከርካሪ ከሰል ጭኖ ለሽያጭ ሲያጓጉዝ በፖሊስ የተያዘ ሲሆን በኢሉባቡር ቡሬም ከ320 ጄሪካን በላይ የእርዳታ ዘይት በኮንትሮባንድ ለመሸጥ ሲጓጓዝ የነበረ የመከላከያ ሰራዊት መኪና መያዙን ለማወቅ ተችሏል።

በሌሎች የኦሮሚያ ክልል ከተሞችም ተመሳሳይ የሀዘንና የተቃውሞ ትዕይንቶች መደረጋቸው ታውቋል።

በጨለንቆው ጭፍጨፋ የመከላከያ ሰራዊት ከ20 በላይ ሰዎችን መግደሉ የሚታወስ ነው።

በአማራ ክልል በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው ተቃውሞ በቀጠለበት በዚህን ወቅት የህወሀት መንግስት በአስገዳጅነት ትምህርት ለማስጀመር ጥረት እያደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በዩኒቨርስቲዎቹ ከ70 በመቶ በላይ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣታቸው የተገለጸ ሲሆን መንግስት የፖለቲካ መረጋጋት እንዳለ ለማሳየት በሚል በጥቂት ተማሪዎች የትምህርት ሂደቱ እንዲቀጥል ለማድረግ እየተሯሯጠ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በደብረማርቆስ፣ በደረታቦር፣ በባህርዳና ወልዲያ ዩኒቨርስቲዎች ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ግቢውን ለቀው የወጡ ሲሆን አብዛኞቹ ወደየቤተሰቦቻቸው መሄዳቸው ታውቋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በሰጡት መግለጫ በሀገሪቱ ከሚገኙ 36 ዩኒቨርስቲዎች በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ ያሉት 16 ብቻ መሆናቸውን የጠቀሱ ሲሆን 20 ዩኒቨርስቲዎች ከሂደቱ መውጣታቸው ተገልጿል።

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በተቃራኒው በዩኒቨርስቲዎች የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ዕልባት አግኝቶ በመረጋጋቱ ሙሉ በሙሉ ዩኒቨርሲቲዎቹ ወደ ስራቸው ተመልሰዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓርብ የህወሃት መንግስት በሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በአጠቃላይ የሰዓት እላፊ አዋጅ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።