(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 5/2010)
በሰሜን ጎንደር ጭልጋ ወረዳ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።
በአይከል ከተማ ህዝቡ አደባባይ በመውጣት የህወሃትን አገዛዝ ማውገዙ ታውቋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው በመውጣት ላይ ናቸው። ህወሀት ከስልጣን እንዲወርድ ተማሪዎቹ ጠይቀዋል።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ዛሬም ትምህርት አልተጀመረም። አንድ የመንግስት ተሸከርካሪ ዩኒቨርስቲው ደጃፍ ላይ ወድሟል።
በወልዲያ ከ70በመቶ በላይ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወተዋል። በኡርጌሳ ወሎ ህዝቡ ከአጋዚ ሰራዊት ጋር እንደተፋጠጠ መሆኑ ታውቋል። የሰላም ባስ አውቶብስ ጥቃት እየደረሰበት ነው።
በጭልጋ ወረዳ አይከል ከተማ ነዋሪው ዛሬ ተቃውሞ ሲያሰማ ነው የዋለው።
የመንግስት ሰራተኛ፣ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች በአጠቃላይ የአይከል ነዋሪ ባሰማው ተቃውሞ የህወሀት መንግስት በቅማንትና በአማራ ማህበረሰቦች መካከል ደም ለማፋሰስ የሚያደርገውን ሸፍጥ እንዲያቆም ተጠይቋል።
በኮኪት ከተማም ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን ህዝቡ የስራ ማቆም አድማ በማድረግ የህወሃት አገዛዝ እንዲያበቃ ጥያቄ አቅርቧል።
የህወሀት ታጣቂዎች በርከት ያሉ ሰዎችን ያሰሩ ቢሆንም ተቃውሞው ቀኑን ሙሉ ቀጥሎ መዋሉን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣታቸው ታውቋል። የአገዛዙ ባለስልጣናት የተማሪ ተወካዮችን ያነጋገሩ ሲሆን ተወካዮቹም አገዛዙ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለማስተዳደር የሚያስችል ብቃት ስለሌለው ለምን ለተሻሉ ሰዎች አትለቁም በማለት መጠየቃቸው ተሰምቷል።
የአጋዚ ሰራዊት ወደ ግቢው በመዝለቅ በተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙ ታውቋል። የተማሪዎችን ማደሪያ ሰብሮ በመግባት ከፍተኛ ድብደባ ሲፈጽሙ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ዛሬም ድረስ ትምህርት ያልተጀመረ ሲሆን የአገዛዙ ባለስልጣናት ከአጋዚ ሰራዊት ጋር በመሆን በአስገዳጅነት ትምህርት እንዲጀመር ለማድረግ እየተሯሯጡ መሆኑ ታውቋል።
ሌሊቱን ተማሪዎች ከግቢያቸው ሆነው ሲጮሁ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በአጋዚ ሰራዊት ሳይደበደቡ እንደማይቀር ይነገራል።
በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ከትላንት በስቲያ የተጀመረውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች የታሰሩ ሲሆን ዛሬም የተወሰኑ ተማሪዎች ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው ታውቋል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜናም የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወጥተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በወልዲያ ከ70በመቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲውን ለቀው ወጥተዋል።
አብዛኞቹ ተማሪዎች በወልዲያ ከተማ ነዋሪው ዘንድ ተጠግተው እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን በችግር ላይ እንዳሉ በመግለጽ አስቸኳይ ድጋፍ ተጠይቋል።
ወደቤተሰቦቻቸው እንዳይሄዱ ከወልዲያ ወደተለያዩ መዳረሻዎች የሚያስወጡት መንገዶች እንደተዘጉና መንቀሳቀስ እንዳልተቻሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ከትላንት በስቲያ በተገደሉት ተማሪዎች ምክንያት ዩኒቨርስቲው በአጋዚ ወታደሮች ቁጥጥር ውስጥ መውደቁ ተገልጿል። ተማሪዎች ግን በግቢው እንደሌሉ ታውቋል።
ትናንት ማታ በእናቴ ማርያም ፣ በመድሃኒዓለም ፣ በስላሴ ቤተክርስቲያናት አድረዋል።ዛሬ ቡዙዎቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ተጉዘዋል።
በአፋር ሰመራ ዩኒቨርስቲም ተቃውሞ ሊነሳ እንደሚችል እየተነገረ ነው። ተማሪዎች የጥሪ ወረቀት የበተኑ ሲሆን የአማራና የኦሮሞ ወገኖቻችን በአጋዚ ሰራዊት እየተገደሉና እየተደበደቡ እኛ የምንማርበት ምክንያት የለም በሚል የተቃውሞ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል በወሎ ውጫሌና ኡርጌሳ የተነሳው ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን ትላንት በአጋዚ ወታደሮች የተገደለው ወጣት የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ሲፈጸም ተቃውሞ መደረጉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት ንብረት የሆነው የሰላም ባስ አውቶብስ በተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ጥቃት እየተፈጸመበት እንደሆነ ተገልጿል።