ዚምባቡዌ መንግስቱ ሃይለማርያምን አሳልፌ አልሰጥም አለች

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 5/2010)

ዚምባቡዌ የቀድሞ የኢትዮጵያን ፕሬዝዳንት መንግስቱ ሐይለማርያምን አሳልፋ እንደማትሰጥ አስታወቀች።

የዚምባቡዌ መንግስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለፈው ወር ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን ከተነሱ በኋላ ሀገሪቱ መንግስቱ ሃይለማርያምን ወደ ሀገራቸው እንድትሰድ በመጎትጎት ላይ ናቸው።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ሃይለማርያም አጋርና ወዳጅ የሆኑት ሮበርት ሙጋቤ አሁን በስልጣን ላይ ባይሆኑም ዚምባቡዌ ኮለኔል መንግስቱን አሳልፋ እንደማትሰጥ አንድ የሀገሪቱ ባለስልጣን ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

የዚምባቡዌ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሙጋቤ ተገደው ከስልጣን መልቀቃቸውን ካሳወቁበት ጊዜ ጀምሮ መንግስቱ ሃይለማርያም ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ በመወትወት ላይ ናቸው።

የአዲሱ የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ናንጋግዋ ቃል አቀባይ ጆርጅ ቻራምባ የተቃዋሚዎቹን ጥያቄ አጣጥለውታል።

አያይዘውም ተቃዋሚዎቹ በማያውቁት ጉዳይ ላይ ገብተው የሚፈተፍቱ ናቸው ብለዋል።

ቻራምባ ሲቀጥሉም የኮለኔል መንግስቱ ጉዳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ባለመሆኑ ተቃዋሚዎቹ እዚህ ውስጥ መግባት የለባቸውም ሲሉ ተናግረዋል።

ለመሆኑ የዚምባቡዌ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ እንኳን ተላልፎ ይሰጠኝ ብላ ሳትጠይቅ እነሱ እዚህ ጉዳይ ውስጥ ለምን ገቡ? ማለታቸውን ዴይሊ ኔሽን በዘገባው አስፍሯል።

መንግስቱ ሃይለማርያም እንዴት ወደዚህ ሀገር እንደመጡ እንኳን ተቃዋሚዎች አያውቁም።የእሳቸው ጉዳይ በአለም አቀፍ ሕግና ደንብ የተያዘ ጉዳይ ነው ሲሉ ቃል አቀባዩ አስረግጠው ተናግረዋል።

ቻራምባ ሲቀጥሉም ከሩዋንዳ፣ከኮንጎ፣ከሞዛምቢክ የመጡ ባለስልጣናት እዚህ ሀገር ይገኛሉ ለምን ስለነሱ አያነሱም?ለምን መንግስቱ ብቻ ሲሉ ተደምጠዋል።

ሙጋቤ እኛን ለማጥቃት የሚውሉ ፖሊሲዎችን እንዲያወጡ መንግስቱ ሃይለማርያም ምክራቸውን ለግሰዋል ሲሉ የዚምባቡዌ መንግስት ተቃዋሚዎች ይከሳሉ።

በ1983 ሕወሃት ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ መንግስቱ ሃይለማርያም ወደ ዚምባቡዌ አምርተዋል።

መንግስቱ ሃይለማርያም ኮበለሉ ወይንስ ተገደው ሄዱ የሚለው አሁንም መልስ ያጣ ጥያቄ ቢመስልም የዚምባቡዌው ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ግን ዛሬ አንድ ነገር ፈንጥቀዋል።

ኮለኔሉ ዚምባቡዌ የሄዱትና የሚቆዩት በአለም አቀፍ ሕግና ደንብ ስምምነት መሰረት ነው የሚል።

ከሁለት አመት በፊት አንድ የዚምባቡዌ ጋዜጣ ኮለኔል መንግስቱ የዚምባቡዌ ወታደራዊ ባለስልጣናት አማካሪ ናቸው ሲል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ደግሞ ባለፈው ሳምንት ዕትሙ በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ ሰዎችን አናግሮ ባወጣው ዘገባ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ እንዲሁም መንግስቱ ሃይለማርያም ምንም ያድርጉ ምን ለሀገር አሳቢነታቸው ጥያቄ ውስጥ የማይገባ በመሆኑ አንዳንድ ሰዎች ያለፈውን ስርአት ይናፍቃሉ ሲል ጽፏል።

መንግስቱ ሃይለማርያም ስልጣኑን በያዘው የሕወሃት አገዛዝ ፍርድ ቤት በሌሉበት የእድሜ ልክ እስራት እንደተበየነባቸው ይታወሳል።