(ኢሳት ዜና–ሕዳር 25/2010)
የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ በመሆን በቅርቡ የተመረጡት የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ የበላይነት የሚባል ነገር የለም ሲሉ አስተባበሉ።
አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ የበላይነት አለ ማለት ልጆችን አያ ጅቦ መጣብህ እያሉ እንደማስፈራራት ይቆጠራልም ብለዋል።
የአማራና የኦሮሞ ሕዝን እሳትና ጭድ ናቸው በማለት የሚታወቁት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ የበላይነት አለ በሚል የተነዛው የፈጠራ ወሬ አደገኛ ውጤት አስከትሏል ሲሉም በሀገር ውስጥ ካለ አንድ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገለጸዋል።
የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ የህወሃት ስራ አስፈጻሚ አባል ሆነው ከተመረጡ በኋላ በሰጡት መግለጫ የህወሃት አመራር ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ተገልጋይ ሆኗል ብለዋል።
የቀድሞው አመራር ወደ ጥገኛ ገዥ መደብነት በመሸጋገሩ ህዝብን ክዷል ሲሉም አቶ ጌታቸው የአገዛዙ ደጋፊ ከሆነ አንድ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳሉት ከህወሃት የተባረሩት የስራ አስፈጻሚ አባላት በግምገማ ወቅት የቀረበባቸውን ችግር እንዲያርሙ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልሆኑም።
እናም በዚሁ ሳቢያ ርምጃ ተወስዶባቸዋል ነው ያሉት።
አቶ ጌታቸው የትግራይ የበላይነት አለ ስለሚባለው ነገር ምን ይላሉ ተብለው ለተጠየቁትም ይህ ውሸት ነው ሲሉ በንዴት አስተባብለዋል።
የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲ ተነፍጎታል፣መሃል ሀገር ካለው ዜጋ በላይ እየተረገጠ ነው ይባላል ለተባሉት ግን ሁኔታው ይስተካከላል በማለት ሕዝቡ ይህንን ጥያቄ እንደሚያነሳ ገልጸዋል።
የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ እሳትና ጭድ ናቸው።እኛ የሚጠበቅብንን ስራ ባለመስራታችን ተባበሩብን በማለት የሚታወቁት አቶ ጌታቸው ረዳ ለተቃውሞ የወጣን ህዝብ ጋኔል በማለት መሳደባቸውም ይታወሳል።