(ኢሳት ዜና–ሕዳር 22/2010)
የፕሬዝዳንት ትራምፕ የቀድሞ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ማይክል ፍሌን ዛሬ በፍርድ ቤት ጥፋተኝነታቸውን አመኑ።
ማይክል ፍሌን በፍርድ ቤት ቀርበው የሀገሪቱ የፌደራል ምርመራ ቢሮ/ኤፍ ቢ አይ/ ጉዳዩን በተመለከተ ባደረገላቸው ምርመራ መዋሸታቸውን አምነዋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ማይክል ፍሌን ሩሲያ ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች በሚል የፌደራል ምርመራ ቢሮ/FBI/ ምርመራ ሲያደርግላቸው በወቅቱ የሰጡት ቃል ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ጥፋታቸውን አምነዋል።
ማይክል ፍሊን በዋሽንግተን ዲሲ ከሩሲያ አምባሳደር ጋር በፈረንጆቹ 2016 የአሜሪካ ምርጫ ወቅት በድብቅ ተወያይተዋል በሚል በምርመራ ቢሮው በተጠየቁበት ወቅት መዋሸታቸውንና ይህም ጥፋት ነው ሲሉ ለፍርድ ቤት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ማይክል ፍሌን ጥፋተኛ ከተባሉባቸው ጉዳዮች መካከል በዋሽንግተን ዲሲ ከሩሲያ አምባሳደር ሰርጌ ኪስሊያክ ጋር በወቅቱ የኦባማ አስተዳደር በሩሲያ ላይ የጣላቸውን ማዕቀቦች በተመለከተ ጉዳዩን ከማባባስ ሩሲያ እንድትቆጠብ የጠየቁበትና አምባሳደሩ የተስማሙበት ጉዳይ አንዱ ነው።
ሌላው በኦባማ አስተዳደር የተደገፈውና ባለፈው አመት መጨረሻ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እስራኤል የፍልስጤምን ግዛት መቆጣጠሯ ሕጋዊ አይደለም የሚለውን የድምጽ ውሳኔ ሩሲያ እንድታዘገይ መጠየቃቸው መሆኑ ታውቋል።
በሮበርት ሙለር የሚመራውና ሩሲያ ባለፈው የአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች የሚለውን ጉዳይ የሚመረምረው ቡድን መጀመሪያ ያነጣጠረው በእኚሁ የቀድሞ የጸጥታ አማካሪ ላይ ነበር።
ጥፋተኝነታቸውን ዛሬ ያመኑት ፍሊን አድራጎታቸው ትክክል እንዳልነበርና ለሙለር ምርመራም እንደሚተባበሩ አረጋግጠዋል።
ፍሊን ባለፈው ምርጫ ወቅት በፕሬዝዳንት ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ከተከሰሱት ውስጥ አራተኛ ሰው መሆናቸው ነው።
የትራምፕ ምርጫ ዘመቻ ሊቀመንበር ፖል ማናፎርትና ምክትላቸው ሪክ ጌትስ ጥፋተኛ አይደለንም ማለታቸው ይታወሳል።
የትራምፕ የምርጫ ቡድን የውጪ ፖሊሲ አማካሪ ጆርጅ ፓፓዶፓሉስ ግን በኤፍ ቢ አይ ከሩሲያ መንግስት ጋር ግንኙነት አድርገሃል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አዎ ጥፋተኛ ነኝ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የዛሬው የፍሊን ጥፋተኝነታቸውን ማመን ለፕሬዝዳንት ትራምፕና ለአስተዳደራቸው መጥፎ ዜና ሆኗል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቀድሞውን የኤፍ ቢ አይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሚን በፍሊን ላይ የሚደረገው ምርመራ እንዲቆም ጠይቀው እንደነበርና በኋላም ምርመራው በመቀጠሉ ትራምፕ ዳይሬክተሩን እንዳባረሯቸው ይታወሳል።
ፍሊን ጥፋተኝነታቸውን ማመናቸውና ከመርማሪው ቡድን ጋር መተባበራቸው ወደፊት የሚመጣውን ቅጣት ለማቅለል እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን ለማጋለጥ ፍቃደኛ መሆናቸውን ያሳያል ሲሉ በአሜሪካ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።
አሁን ለትራምፕ አሳሳቢ ሊሆን የሚችለው በሙለር እየተደረገ ያለው ምርመራ በዋናነት ፍሊንና ሌሎች የፕሬዝዳንቱ የምርጫ ዘመቻ አማካሪዎች ላይ ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑ ነው።
ረጅም ማጥመጃውን ዘርግቶ ሁሉንም አሳዎች ለመያዝ ያለመ መሆኑና ለጊዜው ትልቅ የተባለውን አሳ ማጥመዱ ነው።