አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች በመከላከያ ሃይል እንዲጠበቁ ተደረገ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 22/2010)

በኦሮሚያ ክልል ያሉ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች በመከላከያ ሃይል እንዲጠበቁ መደረጉ ተሰማ።

የፖሊስ ሃይሉን ገሸሽ ያደረገ ይህ ተግባር ምናልባትም አመጽ እያሰማ ያለውን ህዝብ በሃይል ለማፈን የተቀነባበረ ሴራ መኖሩን እንደሚያሳይ ምንጮች ገልጸዋል።

በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም ግቢዎቻቸውን እየለቀቁ በመውጣት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትላንት በስቲያ በአዳማ ናዝሬት ስኳር ጭኖ ሲንቀሳቀስ የነበረ አንድ የጭነት ተሽከርካሪ በህዝብ ቁጥጥር ስር ውሏል።

የሕወሃት አገዛዝ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ለተቀሰቀሰው አመጽ ማሰሪያ ያጣለት ይመስላል።

ለዚህ ማሳያ ደግሞ ከሕብረሰቡ ወጥቶ ህብረሰቡን እየደበደበ አልያም እየገደለ ያሳምንልኛል ያለውን የፖሊስ ሃይል ገሸሽ በማድረግ የመከላከያ ሃይሉ ሁሉንም አካባቢዎች እንዲቆጣጠር እያደረገ መሆኑን ነው የኢሳት መረጃዎች ያመለከቱት።

የፖሊስ ሃይሉን ገሸሽ ያደረገው ይህ ተግባር ምናልባትም አመጽ እያሰማ ያለውን ህዝብ በሃይል ለማፈን የተቀነባበረ ሴራ መኖሩን የሚያሳይ ነው ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ያሉ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በመከላከያ ሃይል እንዲጠበቁ መደረጉ ተሰምቷል።

እንደ ኢሳት ምንጮች ከሆነ የመከላከያ ሃይሉ ዩኒቨርስቲዎችን ብቻ ሳይሆን በምስራቅ ሀረርጌና በሌሎች አካባቢዎች የሕዝብ አመጽ ይቀሰቃሳል ተብሎ የሚሰጋባቸውን አካባቢዎች ወሯል።

በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች ተቋማቱን እየለቀቁ በመውጣት ላይ ናቸው።በየዩኒቨርስቲዎቹ የቀሩት ተማሪዎችም ቢሆኑ በጣም ጥቂት የሚባሉ መሆናቸው ታውቋል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ጦር ወደ ኦሮሚያ ክልል እየገባ የሚያደርሰውን ጥቃት ያቁም፣ የዜጎችም ግድያ ይቁምና ሌሎች ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ ሲያነሱ የነበሩት ተማሪዎች ምላሽ የሚሰጣቸው ቢያጡ የትምህርት ገበታቸውን ጥለው ለመውጣት ተገደዋል።

ከነዚህ ውስጥ የአምቦ፣የመቱና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ ወቶበታል የተባለው የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ይገኙበታል።

የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በመከላከያ ሃይሉ እንዲጠበቁ ተደርጓል።ተማሪዎቹ ግን ግቢያቸውን ጥለው መውጣታቸውም ተሰምቷል።

የተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀል ደግሞ በአምቦ ከተማ ሌላ ህዝባዊ አመጽ እንዲቀሰቀስ ምክንያት እየሆነ ነው ይላሉ ምንጮቹ።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ላይ አላግባብ የሚደርሰው በደል ያልተዋጠላቸው የአምቦ ከተማ የሁለተኛ እና የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ወደ ከተማዋ በመውጣት ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ የከተማዋ ህዝብም ተቀላቅሏቸዋል።

በከተማዋ የተሰማራው የመከላከያ ሃይሉም የጭካኔ ተግባሩን ሊፈጽም በዝግጅት ላይ ስለመሆኑ ምንጮቹ አረጋግጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ከትላንት በስቲያ በአዳማ ናዝሬት ስኳር ጭኖ ሲንቀሳቀስ የነበረ አንድ የጭነት ተሽከርካሪ በህዝቡ ትብብር በቁጥጥር ስር እንዲውልና ህዝቡ ስኳሩን እንዲከፋፈል ተደርጓል።

ህወሃት በየጊዜው የሚፈጽመውን አላግባብ ዝርፊያና የማናለብኝ ተግባር የማሰናከሉ ስራ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የአዳማ ነዋሪ ወደ አሰላ የሚወስደውን ዋና መንገድ በድንጋይ በመዝጋት ባደረገው ተቃውሞ በ2 ኦራል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ተጭኖ የነበረውን ስኳር ማገዱንና ህዝቡ እንዲከፋፈለው መደረጉን ኢሳት ባለፈው ረቡዕ መዘገቡ ይታወሳል።